ስንክሳር View RSS

No description
Hide details



የሒንዱኢዝም እግረኛ ወታደሮች 28 Feb 6:23 AM (14 days ago)

ሕንድን የተመለከተው መጣጥፍ በቁም ነበር ከመጀመሩ በፊት በ 2001 ሕንድን ስጎበኝ ለአንድ ቀን ፣ባረፍንበት የአግራ ሆቴል፣ ሆቴሉ ከተማውን እንዲያሳየን የመደበው አስጎብኚ የነገረንን አስቂኝ ቀልድ ላጋራችሁ፡፡ ቀልዶቹ ስለ ‘’ሲክ’’ ነገድ ናቸው፡፡ ሲኮች ጺህማቸውን የሚያሳድጉ፣ የሆነ የራስ መሸፈኛ በቄንጥ የሚጠመጥሙ፣ ከሕንድ ህዝብ ቁጥር አርባ በመቶውን የሚያክሉ፣ ከሕንድ ሀብታሞች ግን ከግማሽ የሚበልጡት ናቸው፡፡ ሀብታምና ነጋዴነታቸውን በተመለከተ ከኛ ጉራጌዎች ጋር ይመሳሰላሉ፡፡

ታድያ የሕንድ ቀልዶች በብዛት ሲኮች ላይ ያተኩራሉ

አንድ ሀብታም ሲክ አሽከሩ አለምንም ስራ ተቀምጦ ያገኘዋል፡፡

‘’ስራ ጨርሰህ ነው እንደ ሚኒስቴር እግርህን አንዘራፍጠህ የተቀመጥከው?’’ ይለዋል

ቁጭ ብሎ ገንዘቤን እየበላ…ብሎ ቆጭቶታል፡፡ ስራ ሊያዘው ቢፈልግ ምንም ስራ ያጣል፡፡ የሚልከው ነገር የለም፣ ልብሱ ተተኩሷል፣ ቤቱ ጸድቷል….አሀ! አሀ! ግቢው ውስጥ ያለው የአትክልት ስፍራስ? እንዴ፣ እንዴት ረሳሁት

‘’ስማ በል ሂድና አትክልቶቹን ውኃ አጠጣ’’

አሽከሩ ግራ በተጋባ ሁኔታ ሲክ አሳዳሪውን እየተመለከተ

‘’ እንዴ ጌታዬ ዝናም እየዘነበ’ኮ ነው’’ ይለዋል፡፡ ሲኩም

‘’ታድያ የዘነበ እንደሆንስ? በል፣ ቶሎ በል፣ ሰነፍ፡፡ ዣንጥላውን ራስህ ላይ አድርገህ አትክልቱን ውኃ አጠጣ!’’

generated by AI

ዛሬ የምናወራው ስለ ራሽትሪያ ስዋያሜቫክ ሳንግህ ወይም ካሁን ወዲያ በማሳጠር RSS  ስለምንለው የሒንዱ አክራሪ ብሔራዊ ድርጅት ነው፡፡ አባላቱ ካኪ ሱሪ፣ እጅጌው የተጠቀለለ ነጭ ሸሚዝ ይለብሳሉ ጥቁር ቆብ ይደፋሉ፡፡ የ RSS ሰዎች ባለ ጢም ወጣቶች፣ ቦርጫቸው ትንሽ ገፋ ያለ ባለመካከለኛ እድሜ ወንዶች፣እንዲሁም መነጽራቸው አፍንጫቸው ላይ የተደፋ አረጋውያን ናቸው፡፡ ሴት አባላት የሉትም፡፡ (The Economist, December 21st 2024)

ድርጅቱ ከአምስት ሚሊዮን በላይ አባላት አሉት፡፡ በአለም ላይ በፈቃደኞች የተመሰረተ ትልቁ ቡድን ነው፡፡ የበጎ አድራጎት ስራዎችን ያከናውናል በተጨማሪም ወጣቶችን ስነስርአት ያስተምራል፡፡ በስነስርአት ተሰልፈው የሚያወጡት እና የሚያወርዱት ብርቱካንማ ሰንደቅ ዓላማ አለው፡፡ ተቃዋሚዎቹ ይህ ትምክህተኛ ቡድን የሕንድ ህዳጣን ማህበረሰቦችን ይተናኮናል ይሉታል፡፡ ዋና መቀመጫው ናግፑር በተባለችው ከተማ ነው፡፡ (ዝኒ ከማሁ)

 RSS የተመሰረተው በእንግሊዝ የቅኝ አገዛዝ ዘመን በ 25 ሰፕተምበር 1925 ነው፡፡ አላማው በስነስርአት የታነጸ እና ለ‘’የሒንዱ ትንሳዔ’’ የቆመ የፈቃደኞች ድርጅት መስርቶ ሒንዱ ራሽትራ ወይም ‘’የሒንዱ አገርን’’ መመስረት ነው፡፡ (The Diplomat By Snigdhendu Bhattacharya፣ September 30, 2024)

እንደተቀሩት ክለባት ሁሉ RSSም የተመሰረተው በልምዶች፣ስርአተ-አምልኮቶች፣ እና ጌጣጌጦች ነው፡፡ ወጣት ሕንዳውያን ከመዳህ ወጥተው መራመድ እና መናገር ሲጀምሩ ይቀላቀሉታል፡፡ እነሱም ወደ መሰብሰቢያ እና መለማመጃ ካምፖቹ በየእለቱ ይሄዳሉ፡፡ ብዙዎቹ ጓደኞቻቸውን ለመጠየቅ እና ትንሽ ስፖርት ለመስራት በወጡ ወላጆቻቸው ነው ወደ እዚያ መሄድ የሚጀምሩት፡፡ ሁሉም አባላት የ RSS ስግደቶችን፣ መዝሙሮችንና ጨዋታዎችን ይማራሉ፡፡ በተለይ የደንብ ልብሳቸው በመላው ሕንድ የታወቀ ነው፡፡ (The Economist)

በ RSS ቡድን በጣም ትልቁ ድግስ የሒንዱው ዱሴሀራ በዐል ሲሆን ይህም ቀን በተመሳሳይ ድርጅቱ የተመሰረተበት እለት ነው፡፡ የ2024ቱ በዐል ደሞ የራሽትሪያ መቶኛ አመትም ስለሆነ ልዩ ነበር፡፡ በመቶ ሺህ የሚገመቱን የ RSS ሰልፈኞች እየተመሙ ቦታቸውን ሲይዙ፣ ሞሀን ብሃግዋት የተባለው በሰባዎቹ ውስጥ የሚገኘው ስድስተኛው መሪያቸው መድረኩን ይይዛል፡፡ እሱም ከውጭ ሙስሊሟ ፓኪስታን፣ እንዲሁም ከውስጥ ‘‘ስውር መንግሥት’’፣’’የመብት ታጋዮችን፣ እና ‘’መደበኛ ማርክሲስት’’ የተሰኙ ውስጣዊ ጠላቶች በሕንድ ላይ ስላሰፈኑት ስጋት በስሜት ተናገረ፡፡ አባላቱንም የሚያስፈልጋቸውን ሁሉ ከአገር ውስጥ ምርቶች እንዲገዙ፣ እንዲሁም ባህላዊ አለባበሳቸውንና ቋንቋቸውን ጠብቀው መዝለቅ እንዳለባቸው አሳሰበ፡፡ ‘’ዓለም ኃየይለኞችን አምላኪ ናት፣ ደካማ ሁሌም የተናቀ ነው’’ አለ በስሜት፡፡(ዝኒ ከማሁ)

ከ RSS መጠጋት ከኃይል ጋር መጠጋት ነው፡፡ በዚያ ስብሰባ ላይ የሕንድ የሕዋ ሳይንስ የቀድሞ ኃላፊና ቢያንስ አንድ ቢሊዮኔር ተገኝተዋል፡፡ በዚህ ንግግሩ የ RSS መሪ፣ የሕንድ ጠቅላይ ሚኒስቴር ናሬንድራ ሞዲን ቢያሞጋግስ እንዳይገርማችሁ፣ምክንያተም ናሬንድራ ናዲ የድርጅቱ አባል ነውና፡፡ ገና በስምንት አመቱ ነበር የአሁኑ የሕንድ ጠ/ሚ ቡድኑን የተቀላቀለው፡፡ ፖለቲካ ውስጥ ከገባ እስከ ሰላሳ አመቱ ድረስ የ RSS  ቋሚ ሰራተኛ ወይም ፕራቻራክ ነበር፡፡ የዚህ ድርጅት ሙሉ አባልነት ንብረትን መተው/መናቅ እና ከወሲብ መቆጠብንም እንደሚጨምር እያሰላሰላችሁ፡፡ ናሬንድራ ሞዲ ጠ/ሚ ሆኖ ከተመረጠ አንስቶ ካቢኔውን ያዋቀረው በብዛት በ RSS ሰዎች ነው፡፡(The Economist)

የ RSS ሰልፍ                                                       India today

እንዴት አንድ ባህላዊ የሆነ፣ ቀላል ኑሮን የሚከተል ቡድን ይህን ያህል ተከታይ ሊኖረው ቻለ? ምክንያቱ የሚመነጨው ቡድኑ የሚያቀነቅነው ሀሳብ ለሒንዱዎች ቀላልና ውስጣዊ ስለሆነ ነው፡፡ ይህንኑ ቡድን ለአጭር ጊዜ ተቀላቅለው በኃላ ግን የለቀቁት፣ በአሁኑ ግዜም ዋና ተቺው፣ ‘’ፑራሾታም አግራዋል’’ ስለዚህ ጉዳይ ተጠይቀው ሲመልሱ.

‘’ የ RSS ቡድን ማለት ፓርቲው፤ ወጣት ሰዎችን ወጣትነታቸው ሳያግዳቸው፤ አረጋውያኑን ደሞ የቤተሰብ ኃላፊነታቸው ሳይወስናቸው፣ ለሕንድ ብሄር አስተዋጽዖ ለማረግ እንደሚችሉ እንዲሰማቸው ስሚያደርግ ነው’’ ብለዋል(ዝኒ ከማሁ)

እስቲ አሁን ደሞ የቴፓችንን ክር ወደኃላ በፍጥነት እናጠንጥን፡፡ ኬስሀቭ ባሊራም ሄድጌዋር የተባለ ዶክተር እና ፖለቲከኛ በ 1925 ዓ.ም. በናግፑር ከተማ ራሽትሪያን መሰረተ፡፡ እሱና ተከታዮቹ ሕንድ ታላቅ መሆኗን ሰበኩ፡፡ በውጪ ወራሪዎች ስልጣኔዋ ስንኩል ሆነባት እንጂ ሕንድስ ታላቅ ሀገር ነበረች፡፡ እነዚህ የውጭ ወራሪዎች መጀመርያ በ አስራስድስተኛው ክፍለ ዘመን ሙግሀሎች፣ በአስራ ስምንተኛው ክፍለ ዘመን ደሞ ታላቋ ብሪታንያ ናቸው፡፡ አሁን በሕንድ የሚገኙት 15 መቶኛ ሙስሊሞች የሙግሀሎች የልጅ ልጆች እንጂ ሕንዳውያን አይደሉም፡፡ ለፓኪስታን እንደ አምስተኛ ረድፍ ሆነው የሚያገለግሉ የውስጥ ጠላቶች ናቸው፡፡ ስለማይታመኑም ወደ ንጹህ የሒንዱ ላሞችም ሆነ ልጃገረዶች አካባቢ ድርሽ ማለት የለባቸውም፡፡ የዚህ ዶክተር ዋና አላማ ስነስርአት ያላቸው የሒንዱ አርበኛ ካድሬዎችን መፍጠር እና ሕንድን የሒንዱዎች ብቻ ሀገር ማድረግ ነው፡፡ (ዝኒ ከማሁ)

ሄድገዋር RSS  የባሕል እንጂ የፖለቲካ ድርጅት እንዲሆን አልነበረም የፈለገው፡፡ ይሁን እንጂ ተከታዮቹ በሕንድ ነጻነት ወቅት አገሪቱ ለሁለት መከፈሏ አስደነገጣቸው፡፡ የሕንድን ባለ ሶስት ቀለም ሰንደቅ አላማ አልተቀበሉም፡፡ ለነሱ የሕንድ ምልክት ሳፍሮን (ብርቱካንማ) ነው፡፡ አለማዊ የሆነውን የሕንድን ሕገመንግሥት ጭራሹኑ አልተዋጠላቸውም፡፡

Mohandas Karamchand Gandhi

በ 1948 የ RSS የቀድሞ አባል የሆነው ናቱርማን ጎድሴ የሕንድ አይነተኛ መሪ የሆነውን ማህተማ ጋንዲን ገደለው፡፡ ለድርጊቱ የሰጠው ምክንያት ከ RSS  ሀሳቦች ጋር ፍጹም ተመሳሳይ ነበር፡፡ ጋንዲ ‘’ሙስሊሞችን አባብሏል፣ አለማዊ የሆነ ሕገመንግስትን ደግፏል፣ ፓኪስታንም ከሕንድ ተገንጥላ መንግሥት እንድትሆን ደግፏል’’ የሚል ነበር፡፡ የ RSS ቡድን በግድያው እንደሌለበት ቢገልጽም መንግሥት ለአመት ያህል እንዳይሰራ አግዶት ነበር፡፡ ከዚህ በኃላ RSS  መሪዎች የፖለቲካ ክንፍ አቋቁመው መንቀሳቀስ ጀመሩ፡፡ ከዚህም ብሀራቲያ ጃንታ ፓርቲ (BJP) ተወለደ፡፡

ከ 2014 ጀምሮ ሕንድን የሚመራው ይህ ፓርቲ ነው፡፡

በአሁኑ ጊዜ RSS በሕንድ

በውጭ የሚገኙ ደጋፊዎቹ በብሪታያ፣ አሜሪካ እናም ሌሎች ቦታዎች ስብሰባዎችን ያካሂዳሉ፡፡ የህንድ ብዩራን (ዲያስፖራ) ግን ስለ ቡድኑ ሲጠየቁ ፊት ለፊት ከመደገፍ ሲቆጠቡ ይታያሉ፡፡ መሪዎቹ የገቢ ምንጫቸው በስጦታ የሚገኝ ነው ቢሉም ፋይናንሱ ግልጽ አይደለም፡፡ በሰፊው በዘረጋቸው መረቦች በሁሉም የሕንድ ክፍሎች ትልቅ ተጽዕኖ ያለው ፓርቲ ነው፡፡

RSS በሕንድ የፖለቲካ ህይወት ላይ ስላመጣው ለውጥ የሕንድ ኮንግረስ ፓርቲ መሪ እንዲህ ይላሉ –

‘’የሕንድ ዲሞክራሲያዊ ውድድር ባሕርይ ፈጽሞ ተለውጧል፡፡ ይህም የሆነው አክራሪ እና ፋሽሽታዊ በሆነው ራሽትሪያ ሰዋያምሴቫክ ሳንግህ ድርጅት ባከናወነው ስራ ነው፡፡ይህ ድርጅት በሕንድ ከሚገኙ ዋና ዋና ተቋማት አብዛኞቹን በሚባል ደረጃ የተቆጣጠረ ነው’’ ራሁል ጋንዲ በ 2023 እንደተናገሩት (The diplomat)

በጠቅላላው ፓርቲው ከ 73000 በላይ ቅርንጫፎች ወይም ሻክሀ አሉት፡፡  አባላቱ በየቀኑ በየመናፈሻው፣ በየቴምሉ ለአንድ ሰዐት ይገናኛሉ፡፡ መጀመርያ ዮጋ ይሰራሉ ቀጥለውም ባህላዊ ስፖርቶችን ይጫወታሉ፡፡ በመጨረሻ በታሪክ እና ፍልስፍና ላይ ያተኮረ ትምህርት ይሰጣል፡፡የየቡድኑ መሪዎች በስራቸው ቀልድ አያቁም፣ በተለይ በስነስርአት ደካማ በሆኑ ወጣቶች ላይ ጥብቅ ናቸው፡፡ የሻክሀ ሞዴል ለመገናኛ ጠቃሚ ነው፡፡ በኮቪድ ዝግ ወቅት ግንኙነቶች በርቀት ዋትስአፕን በመጠቀም ቀጥለው ነበር፡፡ በባንግሎር ሻካሀ ስብሰባዎቹን እሁድ ጠዋት ነበር የሚያደርገው፡፡ የሕንድ ሲልከን ቫሊ ነዋሪዎች በስራ የተወጠሩ ስለሆኑ፡፡ ምንም እንኳ ሻክሀ ሒንዱ እና ሳነሰከሪትን የሚያጠብቅ ቢሆንም ስብሰባዎቹ በእንግሊዝኛ ናቸው፡፡ ሁሉንም ሕንዳውያንን ለማሳተፍ፡፡ (The Economist)

ጎልዋልካር የምትባለዋ አይነተኛ የ RSS መሪ በተለይ በነጻነት ትግሉ ትልቅ ቦታ የነበራት ሰው ነች፡፡ ይቺው ሰው ግን የናዚ ጀርመንን ጸረ ሴማዊ ትርክት ደግፋ በመናገሯ አለምን አስደንግጣ ነበር፡፡

በአሁኑ ወቅት እጅግ የሚፈራው የ RSS አካል ቪሽዋ ሒንዱ ፓሪሻድ (VHP) የሚባለው ነው፡፡ ስሙ የአለም ሒንዱ ድርጅት እንደማለት ነው፡፡ የዚህ አካል ወጣት ክንፍ ሙስሊም እና ክርስትያኖች የሒንዱ ልጃገረዶችን ያጠምዳሉ በሚል የሴራ ነቢብ ይመራሉ፡፡ አንዳንዴም ሙስሊም እና ክርስትያን ወጣቶችን ያጠቃሉ፡፡

በሕንድ ታሪክ ታላቁ የጅምላ ጸረ-ሙስሊም ጭፍጨፋ በ 2002 ጉጅራት ውስጥ ተፈጽሟል፡፡ በዚህም ከአንድ ሺ በላይ ሰዎች ተገድለዋል፡፡ ፖሊስ ጭፍጨፋውን የ VHP ቅርንጫፍ መሪዎች ድርጊቱን እንደመሩ ገልጸዋል፡፡ አንዱ መሪ እንዴት ሙስሊሞችን እንዳቃጠለ እና የነፍሰጡር ሴትን ሆድ እንደቀደደ በኩራት ሲናገር በቴፕ ተቀድቷል፡፡ በዚያን ግዜ የጉጅራት ክልል ዋና ኃላፊ የሆኑት ናሬንድራ ሞዲ ወንጀል ፈጻሚዎች እንዳይቀጡ አድርገዋል ተብለው ተከሰው ነበር፡፡ በመጨረሻ ግን የከፍተኛው ፍርድ ቤት  ነጻ አድርጓቸዋል፡፡ (ዝኒ ከማሁ)

የዚህ ድርጅት የኃይል እርምጃ ሰለባ ከሆኑት አንዱ የሕንድ ሙስሊሞች ናቸው፡፡ ካናዳ በሚገኘው ማህበራቸው አማካይነት RSSን የሚመለከቱ ጽሁፎችን ያወጣሉ፡፡ ከነዚህ በአንዱ ስለ RSS የሚከተለውን ይላሉ

‘’ RSS  ወይም ራሽትሪያ ስዋያምሴቫክ ሳንግህ፣ በአለም ላይ ከሚገኙ መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች የበለጠ ተጽዕኖ ያለው ድርጅት ነው፡፡ RSS  የሕንድ ገዢ ፓርቲ ብሀራቲያ ጃናታ ፓርቲ ወይም ቢጂፒ ወላጅ ድርጅት ነው፡፡ ግን ከሕንድ ውጪ ስለሚያራምዳቸው ሀሳቦች ሆነ አጀንዳዎች እምብዛም የታወቀ አይደለም’’’ (National Council Canadaian Muslims (NCCM) : RSS Network in Canada)

 RSS በአሁኑ ወቅት ሰላማዊነቱን በአጽንዖት እየገለጸ ነው፡፡ የቀድሞ መሪዎቹ ስለ አውሮፓ ናዚዎች ከሰጡት አስተያየት ራሱን ሲያርቅ ይስተዋላል ነው፡፡ ይልቅስ የ RSS መሪዎች ቡድኑ ስለሚያከናውነው የበጎ አድራጎት ስራዎች መናገር ይቀናቸዋል፡፡ እነዚህ የበጎ አድራጎት ስራዎች በአጠቃላይ 52500 ሲሆኑ ት/ቤቶች እና ክሊኒኮችን ያቅፋሉ፡፡ ሱኒል አምቤካር የተባሉት የ RSS መሪ ድርጅታቸው የሁሉንም እምነት ሰዎች እንደሚቀበል ቢናገሩም፣ ስንት ሒንዱ ያልሆኑ አባላት እንዳሏቸው ግን አልገለጹም፡፡ በእርግጥም አላማቸው ሕንድን እንደ ሒንዱ ብሔር ማዋቀር ነው፡፡ ግን ድርጅታቸው ሒንዱዎችን የሚተረጉመው  እንደ ‘’ሒንዱስታን’’ (ማለት ለሕንድ የተሰጠ የሒንዱ ስም) መሆኑን፣ ይህም ማለት የሕንድን የአኗኗር መንገድ የሚከተሉትን ሁሉ መሆኑን ይናገራሉ፡፡ (The Economist)

ሕንዳውያንን ለማስተባበር የካስት ክፍፍልን ለማስቀረት እንደሚሰሩ ይናገራሉ፡፡ ይህ ግን በቃል እንጂ ቀላል የሚሆነው በተግባር አይመስልም፡፡ ብሀንዋር ሜግህዋኒሺ የአይነኬው ካስት አባል ነው፡፡ RSS ንም ተቀላቅሎ ነበር፡፡ በሙያው ወጥ ቤት የሆነው ይህ ሰው ያዘጋጀውን ምግብ ለመብላት ሌሎቹ ፍላጎት እንደሌላቸው ሲረዳ RSS ን ለቆ ወጥቷል፡፡

ሕንድ እጅግ ሰፊና በጣም የተለያዩ ማህበረሰብ ያላት እንደመሆኗ፣ በቀላሉ  እንደ ኢራን ቲዎክራሲን (የአንድ ኃይማኖት አገዛዝ) ለማስፈን ታስቸግራለች፡፡ ይሁን እንጂ ጠ/ሚኒስትሩ የጃሙ እና ካሽሚርን ራስ ገዝነት በማስቀረት ለሒንዱስታን የሚያደላ የዜግነት ሕግ አውጥተዋል፡፡ የሕንድ በርካታ ግዛቶችም ከብቶችን በማረድና ኃይማኖትን በመቀየር ረገድ ጠበቅ ያሉ ሕግጋትን ደንግገዋል፡፡ ሚስተር ሞዲ እራሳቸው፣ በ 1992 ደም ባፋሰሰ ረብሻ በወደመው መስጊድ ፍርስራሽ ላይ የሒንዱ ምኩራብን ከፍተዋል፡፤ ይሁን እንጂ የ ሚስተር ሞዲ ከ RSS ያላቸው ግንኙነት ግልጽ አየይደለም፡፡ በመጀመርያ እና በሁለተኛው ምርጫ ከፍተኛ ድምጽ ሲያገኙ ምስላቸውን በየቦታው በመስቀል ግለሰባዊ ከልት ለመትከል መሞከራቸውን የ RSS  መሪዎች አልወደዱላቸውም፡፡ ምክንያተቱም እንደ እነሱ እምነት ማንም ሰው፣ ጠ/ሚኒስትሩም ቢሆን ከፓርቲው በላይ አይደሉምና፡፡ (ዝኒ ከማሁ)

የሕንድ ጠ/ሚ ናሬንድራ ሞዲ

ይሁንና  RSS የታወቀ እና ኃይለኛ ለመሆን የበቃው በራኔንድራ ሞዲ ስልጣን ላይ መውጣት እንደሆነ የሚናገሩ ብዙ ናቸው፡፡ ‘’ RSS ሊያድግ የበቃው BJP የህንድን ፖለቲካ መቆጣጠር ከጀመረ በኃላ ብቻ ነው፡፡ ((NCCM)

አሁን አሁን በራኔንድራ ሞዲ እና በ RSS መሪዎች መካከል ግልጽ አለመግባባት ይታያል፡፡ በተለይ ከዋናው መሪ ብሀግዋት ጋር፡፡ ብሀግዋት በግልጽ ጠ/ሚኒስትሩን መተቸት ጀምረዋል፡፡ ይሁንና በሶስተኛው ዙር ምርጫ ምንም እንኳ ሞዲ ቢያሸንፉም ፓርቲያቸው የፓርላማ የበላይነቱን አጥቷል፡፡ ይህ ሁኔታ ደሞ ከወዳጆቻቸው የሚቀርቡበት እንጂ የሚርቁበት አይደለም፡፡ ስለዚህም ሞዲ ብሀግዋትን ማግባባት ይዘዋል፤ የደህንነት አጀባቸውን በመጨመርና እንዲሀም እስካሁን ባልተደረገ መንገድ የ RSS አባላት በመንግስት መ/ቤቶች ተቀጥረው መስራት እንዲችሉ አድርገዋል፡፡

ለማንኛውም ሁለቱ ተደጋግፈው መቀጠላቸው አይቀሬ ነው፡፡ ምንም እንኳ ሞዲ በአንዳንድ ግለሰባዊ ከልት ስራቸው RSSን ቢያስቀይሙ፤ አለዚህ ፓርቲ ካድሬዎች የምረጡኝ ዘመቻቸው የተሳካ ስለመሆኑ እርግጠኛ አይደሉም፡፡ RSS አለ ራኔንድራ ሞዲ ይህን ያህል የፖለተካ ድል ሊያገኝ አይቻለውም፡፡ ስለዚህ አንዱ ሌላውን ይፈልገዋል፡፡

ለማንኛውም አስተያየት ካላችሁ itaye4755@gmail.com ላይ እንገኛለን

ምንጭ

National Council Canadaian Muslims (NCCM) : RSS Network in Canada

The Economist, December 21st 2024

The Diplomat By Snigdhendu Bhattacharya፣ September 30, 2024

Add post to Blinklist Add post to Blogmarks Add post to del.icio.us Digg this! Add post to My Web 2.0 Add post to Newsvine Add post to Reddit Add post to Simpy Who's linking to this post?

በዘመነ ዶናልድ ትራምፕ 28 Feb 5:47 AM (14 days ago)

(የአለም አቀፍ ግንኙነቶች አምድ)

አሜሪካ በአለም ከፍተኛ ተጽዕኖ ያላት ልዕለ-ኃያል መንግሥት ናት፡፡ በተለይ እንደ ሀገራችን ባለው ገና በመልማት ላይ ባለ ሀገር የሚኖራት ተጽዕኖ ሊጋነን የሚችል አይደለም፡፡ ስንክሳርም እንዲሁ በየእትሟ ቢያንስ አንድ ከአሜሪካ ጋር የሚያያዝ መጣጥፍ ማቅረቧ የውዴታ እና ጥላቻ ስሜት ሳይሆን የአስፈላጊነት ጉዳይ ነው፡፡

ሰሞኑን የአሜሪካን የውጭ እርዳታ ለ30 ቀን እንዲቆም ተደርጓል፡፡ ዘርፈ ብዙ እርዳታ በጤና እና ምግብ ልማት ያቀርብ የነበረው ዩስ ኤይድ ወይም የአሜሪካ አለም አቀፍ የእርዳታ ድርጅት እንዲሁ ታግዷል፡፡ ይህም እንዲሁ በሀገራችን ችግር ማስከተሉ አልቀረም፡፡ ከዕውቀት ነጻ የሆነው ዶናልድ ትራምፕ ለሰው ልጅ ሊራራ የሚችል ልብም እንዲሁ እንደሌለው እያሳየን ነው፡፡

ሰሞኑን ስለ ፕሬዚዳንቱ የተነገረ አንድ ቀልድ ቀልቤን ስለሳበው ላካፍላችሁ፡፡ ዘራቸው እንግሊዝ፣ ሩስያ፣ ጀርመን እና አሜሪካን የሆኑ የሕክምና ጠበብቶች በአንድ አጋጣሚ ተገናኝተው በየአገራቸው ስለተከናወነው አስገራሚ የሕክምና ስራ የየራሳቸውን እያጋነኑ ይተርካሉ፡፡

የጀመረው እንግሊዛዊው ነው፣ ‘’እኛጋ ያሉ ዶክተሮች አንድ በስቃይ ላይ የነበረ በሽተኛን የታደጉበት ዘዴ ‘’ዋው’’ የሚያስብል ነው፡፡ ታማሚው ጉበቱ ተጎድቶ እየተሰቃየ ነበር፡፡ ዶክተሮቹ ታድያ ከሌላ ጤነኛ ሰው ጉበት ቆርጠው ለታማሚው ያስገቡለታል፡፡ በስድስት ሳምንት ውስጥ ሙሉ ጤነኛ አይሆንላችሁም? አሁን ስራ እያፈላለገ ነው፡፡ አሉ፡፡ ሌሎቹም አድናቆታቸውን ገለጹ፡፡

ከዚያ ጀርመናዊው ቀጠሉና በሚዩኒክ ሆስፒታል የተከናወነውን ተናገሩ፡፡ በሚዩኒክ ጠቅላላ ሆስፒታል በአእምሮ ቁስል የሚሰቃይ ሕመምተኛ ነበር፡፡ በተሳካ ቀዶ ጥገና የሚያመውን ክፍል ቆርጠው አከሙት፡፡ በአራተኛው ሳምንት በሽተኛው እረፍት ከርሞ የተመለሰ ሰው መስሎ፣ ፍጹም ድኖ ቤተሰቡን ተቀላቀለ፡፡ አሁን ስራ እያፈላለገ ነው፡፡

ይኽኛውም እንዲሁ ‘’ይበል’’፣ ‘’ይበል’’፣ ‘’ይበል ግሩም ሰናይ ውዕቱ’’ ተባለ፡፡

ራሽያዊው ዶክተር ከሳቸው በፊት የተናገሩ ጓዶቻቸውን ታሪክ በድጋሚ አድንቀው የራሳቸውን ቀጠሉ፡፡ ሞስኮ ልዩ የልብ ሆስፒታል ግማሽ ልቡ የታወከበት ታማሚ ነበር፡፡ ‘’ታድያ ይኸውላችሁ ዶክተሮቹ ከልብ ባንክ ሌላ ጤነኛ ልብ በቀዶ ጥገና አስገብተውለት ሁን ሙሉ ጤነኛ ሆኖ ወጣ፡፡ አሁን ስራ እያፈላለገ ነው፡፡ እንዳሉ የእንግሊዛዊውና ጀርመን ዶክተሮች የሩስያን ዶክተሮች አድንቀው ሳይጨርሱ አሜሪካዊው ጣልቃ ገባና…

ሁላችሁም የተናገራችሁት አፈጻጸም ጥሩ ሊባል የሚችል ቢሆንም፣ ግና በአሜሪካ ከተከናወነው ጋር ጭራሹን አይወዳደርም፡፡ የአሜሪካን ዶክተሮች ከጊዜው እንተዋቸው፡፡ የነሱን ስራና ውጤት ልንገራችሁ ብል ጊዜም አይበቃም፡፡ የአሜሪካ ተራ ህዝብ ከጥቂት ወራት በፊት አዕምሮም ልብም የሌለው ሰው አለምንም ቀዶ ጥገና ፕሬዚዳንት አድርጓል፡፡ አሁን ሁሉም አሜሪካዊ ስራ ፈላጊ ሆኗል፡፡

ከመመረጡ በፊት ‘’ለአንድ ቀን ብቻ ነው አምባገነን የምሆነው’’ ያለው ሰውዬ ይኸው ወሩን ሙሉ በቀን በቀን ሕጋዊነታቸው የሚያጠራጥር ድንጋጌዎችን እያጎረፈ ነው፡፡ የሚገርመው የሱ ተግባር ሳይሆን፣ ድርጊቱን ለመቃወም የነበረው ዝምታ ነበር፡፡

እስቲ መጀመርያ ትራምፕ እየወሰዳቸው ያሉ እርምጃዎችን ለመቋቋም የተደረጉ እርምጃዎችን እንመልከት፡፡

በተመረጠ በነጋታው አሜሪካን ከተባበሩት መንግሥታት የፓሪስ የአየር ለውጥ ስምምነት አስወጣት፡፡ ይህም ማለት ለዚህ የተባበሩት መንግስታት አንድ አካል እንቅስቃሴ አሜሪካ ታዋጣ የነበረው ገንዘብ (88ሚሊዮን ዶላር) ይቆማል ማለት ነው፡፡ ወዲያውኑ  የብሎምበርግ ኩባንያ አክሲዮን ከፍተኛ ባለድርሻ የሆነው ማይክል ብሉምበርግን ጨምሮ ሌሎች ስማቸው እንዳይጠቀስ ያልፈለጉ ሀብታሞች፣ ይህንኑ የአሜሪካን መዋጮ ከራሳቸው አዋጥተው እንደሚሸፍኑ አሳወቁ፡፡ (284 Media 2025/01/27) በዚህም በተባበሩት መንግስታት የፓሪስ የአየር ለውጥ ስምምነት አስፈጻሚ አካል ላይ ሊደርስ የነበረውን የገንዘብ ችግር ተወግዷል፡፡

ማይክል በሉምበርግ

 በሌላ በኩል ደግሞ  የተለያዩ ፍርድ ቤቶች ትራምፕ አዟቸው የነበሩትን፣ ለምሳሌ…

ትዕዛዛት አግደዋል  (USA Today፣ 08/25/2024 Judges are pausing Trump’s policy changes.) በዚህም ለጊዜውን ቢሆን በነዚህ ትዕዛዛት ሊደርሱ የነበሩት ጉዳቶች ቆመዋል፡፡

የዲሞክራቲክ ፓርቲው በኖቨምበር ከገጠመው ሽንፈት ድንጋጤ ገና ያልነቃ ስለሆነ ይሄ ነው የሚባል ተቃውሞ አላሰማም፡፡

የአሜሪካ ኮንግረስ  ካፒቶል ሂል

በጣም የሚገርመው ግን የሬፓብሊካን ፓርቲ የኮንግሬስ አባላት ለትራምፕ ሙሉ በሙሉ ሊባል በሚችል ሁኔታ መገዛታቸው ነው፡፡ መቸም ትራምፕ እውቀት አነሰው ብንል እንኳ እነዚህ የሬፐብሊካን ሴናተሮች በዚህ ረገድ ችግር ያለባቸው አይደሉም፡፡ ግን ሰውየው ሕገመንግስቱን በመጣስ፣ የፓርላማውን ስልጣን በመተላለፍ፣ መሰረታዊ የሰብአዊ መብት ህጎችን በመረጋገጥ የሚሰራውን ሁሉ በዝምታ እያለፉት ነው፡፡

በእርግጥ ከራሳቸው ፓርቲ የተገኘን ፕሬዚዳንት ተቃዋሚ ሆነው ይንቀሳቀሱ አይባልም፡፡ ነገር ግን የሀገሪቱን ደህንነት ሊጎዱ የሚችሉ ስራዎች ሲፈጸሙ አለመተንፈስ፣ እነሱም የሚደግፉት ሕገ መንግሥት ሲጣስ ተመልካች መሆን፤ የዲሞክራሲ ስርአቶች እዚህም እዚያም ሲረገጡ ድምጽ አለማሰማት፣ የራሱ የፓርላው የስራ ድርሻ ሲወሰድ እያዩ እንዳላዩ መሆን ምን ይባላል?

ከሁሉም ከሁሉም ግን፣ ዝምታቸውን እንኳ ዝም ተብሎ ቢታለፍ፣የፌዴራል ቢሮዎችን ለመምራት ብቁ ያልሆኑ ሰዎች በእጩነት ሲቀርቡላቸው መደገፍ በምንም ምክንያት ይቅር የማይባሉበት ስህተት ነው፡፡

እዚህ ላይ ነገሩን ግልጽ ለማድረግ፣ በአሜሪካ አንድ ፕሬዚዳንት በሚኒስተርነትና ሌሎች ዋና ዋና የመንግሥት መ/ቤቶችን የሚመሩ ሚኒስትሮችን ለሹመት እጩ አድርጎ ለ ሴኔቱ(ፓርላማ) የያቀረባል፡፡ ሴኔቱ የቀረቡለትን እጮዎች ሰነድ ይመረምራል፡፡ ማለት የሕይወት ታሪካቸውን፣ በዚህ ቀደም የጥፋት ሬኮርድ እንዳለባቸው፣ የትምህርት እና የስራ ልምድ መረጃቸውን የይመረምራል፡፡ በዚህ ብቁ ከሆኑ እጩዎቹ ሴኔቱ ፊት ቀርበው የማጣርያ ቃለ መጠይቅ ይሰጣሉ፡፡ ከዚህ በኃላ ሹመታቸውን በድምጽ ብልጫ ያጸድቃል፣ ወይም ይጥላል፡፡

በዚህ የትራምፕ እጩዎች ማጣራት ወቅት አንዳንድ አሉ የሚባሉ የሬፓብሊካን ፓርቲ ሴናተሮችን አፈጻጸም ዘ ዋሽንግተን ፖስት ዘግቦት ነበር፡፡ እስቲ ለናሙና አንዳንዱን እንይ

ለምሳሌ ራሳቸው ሕክምናን ያጠኑት ሴናተር ቢል ካሲዲን እንውሰድ፡፡ ስለ ሕክምና ጠቅላላ ዕውቀት እንኳን የሌለው ጸረ-ክትባት እምነቱን እንደ ደህና ነገር በይፋ እስከማወጅ የደረሰው ሮበርት ኤፍ ኬኒዲ  ለጤና ጥበቃ ሚኒስትርነት ታጭቶ ይቀርባል፡፡ በዚህ ውቅት እኚህ ሴናተር ያቀረቡለት ጥያቄዎች እና የሰጣቸው መልሶች ለቦታው ብቁ እንደማይሆን በፊትም የነበረውን ግምት ሙሉ በሙሉ ያረጋገጠ ነበር፡፡ ሌላ ይቅር ስለ ዋና የሚኒስቴሩ አገልግሎቶች ምንነት አጥንቶ እንዳልመጣ እኚሁ ሴንተር ባቀረቡለት ጥያቄ አረጋግጦ ነበር፡፡

ሮበርት ኬኔዲ ለጤና ጥበቃ ሚኒስትርነት ብቁ ነው ወይ? ተብሎ ድምጽ ሲሰጥ ሴናተር ቢል ካሲዲ በመደገፍ ነበር ድምጽ የሰጡት፡፡ (The Washington Post February 6, 2025)

ቀጥሎ የምናያት ደሞ የሬፐብሊካን ሴናተር ጆኒ ኤርንስት ናት፡፡ እቺ ሴትዮ በመከላከያ ሚኒስቴር በነበረችበት ወቅት ስለሴቶች መብት ሽንጧን ገትራ በመከራከር ስም ያላት፣ ራሷም ኢራቅ ዘምታ በክብር ሜዳልያ የተሸለመች ናት፡፡ ለመከላከያ ሚኒስትርነት እንዲጸድቅ የቀረበው እጩ ፒት ሄግሴዝ የሚባል የፎክስ ኒውስ ጋዜጠኛ የሆነ፣ ሴቶችን በመተናኮል የተከሰሰ፣ በግልጽ በተቀዳ ንግግር ሴቶች በጦርነት ማገልገል አይገባቸውም ብሎ የተናገረ ሰው አሜሪካ ሴኔት ቀርቦ ሚኒስቴርነቱ ጸድቆለታል፡፡ ለዚህም የበቃው የሴናተር ጆኒ ኤርንስት የድጋፍ ድምጽ ታክሎበት ነው፡፡ (ዝኒ ከማሁ)

በዛኛው ተገርመን ብዙ ሳንቆይ

የዚህኛው መባስ አያስቅም ወይ

            (ዘንድሮ ከተባለው የጥላሁን ገሠሠ ዘፈን የተወሰደ፡፡ ግጥም ተስፋዬ ለማ)

አሁን የምናየው ደግሞ የርፓብሊካን ሴናተር ቶድ ያንግ ነው፡፡ እኚህ ሴናተር የባህር ወለድ ጦር ውስጥ የመረጃ ቢሮ መኮንን ሆነው ሰርተዋል፡፡ ጥሩ፡፡ ለብሔራዊ ጸጥታ ዳይሬክተርነት እጩ ሆና የቀረበችው ቱልሲ ጋባርድ፣ ደጋግማ የቭላድሚር ፑቲን እና በሽር አል አሳድ አመለካከቶች የምትደግፍ ናት፡፡ ኤድዋርድ ስኖውደን የተባለው የአሜሪካን ምስጢር ሰነዶች ጸኃይ ላይ ያሰጣ ሰውን ከሃዲ፣ የማስጠንቀቂያ ደወል የሰጠ እንጂ ከሀዲ አይደለም ብላ አስተያየቷን የሰጠች ግለሰብ ናት፡፡ ታድያ በአሜሪካ ምድር ከዚች የተሻለ፣ ሰው ጠፍቶ ቱልሲ ጋባርድ ለዚህ ትልቅ ምስጢራዊ ቦታ፣ ሴናተር ቶድ ያንግ ደግፋት ዳይሬክተር ሆናለች፡፡ (ዝኒ ከማሁ)

ከላይ ለትልልቅ ቦታዎች በእጩነት የቀረቡት ሰዎች ሌላው ሁሉ ቀርቶ የትምህርት እና የስራ ልምድ ዝግጅታቸው ውሱንነት ብቻውን ሊመሩት ለታሰቡት ቦታ ውድቅ ባደረጋቸው ነበር፡፡ እንዲያ ቢሆን’ኮ ሌላ ብቃት ያለው ሬፓሊካን ሰው ሊተካ በቻለ ነበር (እንዲያው ገለልተኛ የሆነ ወይም ወደ ሊበራልነት ያደላል ተብሎ የሚጠረጠረው ቀርቶ)

እንዲያው ሌላ ሌላውን ትተን የኮንግሬሱ መሪ ማይክ ጆንሰንን ጉድ እንስማ፡፡ ትራምፕ ከናትናያሁ ጋር ከተወያየ በኃላ፣ አንድ እውቀት ብቻ ሳይሆን ጤንነት የጎደለው ሀሳብ አቀረበ፡፡ አሜሪካ ሁለት ሚሊዮን የጋዛ ነዋሪዎችን ከቀያቸው ፈንቅላ ታስወጣለች፡፡ ከዚያ ቀጥሎ ጋዛን የቀለጠች የምቾት ባህር ዳር መዝናኛ ታረጋታለች የሚል፡፡ ብዙም ሳይቆይ ሌላውን እንተወውና በመካከለኛው ምስራቅ የትራምፕ ወዳጆች የሆኑት ሳዑዲ አረቢያ፣ ጆርዳን እና ግብጽ  ‘’ ሀሳቡ ወይም የቁም ቅዠቱ የለየለት እብደት ነው’’ ነበር ያሉት፡፡

ይህም ሆኖ ታድያ ከሬፐብሊካን ፓርቲ ሆነው ድምጻቸውን ባመኑበት መንገድ ብቻ ሲሰጡ የከረሙትን ሴናተር ሚች ማክኮኔልን በማድነቅ አምዳችንን እንደመድማለን፡፡እንደመድማለን፡፡

ለማንኛውም አስተያየት ካላችሁ itaye4755@gmail.com ላይ እንገኛለን

Add post to Blinklist Add post to Blogmarks Add post to del.icio.us Digg this! Add post to My Web 2.0 Add post to Newsvine Add post to Reddit Add post to Simpy Who's linking to this post?

C’est Passé     ሁሉም አለፈ 28 Feb 4:48 AM (14 days ago)

ትንሿ ሜትሮፖሊታን – አዋሽ 7 ኪሎ

ክፍል ሁለት

የሸዋና ሐረር መገናኛ ኪዳነ ምህረት አበበች ባቡ ቡና ቤት

ሲመሰረት በዚህ ረዢም ስም የሚጠራው ቡና ቤት፣ ዛሬ ቤቱን የሚያስተዳድሩት የቆርቋሪዋ ልጆች አሳጥረውት ‘’አበበች ባቡ መታሰቢያ ቡና ቤት’’ ይባላል፡፡ ስለ ቅድመ ኢሕአዴግ አዋሽ ስንተርክ ዘለን የማናልፋቸው የዚህ ንግድ ቤት ባለቤት እና መስራች እትዬ አበበች ባቡን ነው፡፡ እትዬ አበበች የአዋሽ ሰፈር አድባር ነበሩ፡፡ ዘለግ ያለ ቁመት ሙሉ ሞንዳላ ሰውነት አላቸው፡፡ መልካቸው ቀይ ሆኖ ጉንጫቸው ሞላ ያለ በመጠኑ ሰልከክ ያለ አፍንጫ ትንንሽ የተስተካከሉ ነጫጭ ጥርሶች ያላቸው መልከ መልካም ወይዘሮ ነበሩ – እትዬ አበበች፡፡

ከጠላት በኃላ አዋሽ በአከባቢዋ ላሉ አርብቶ አደርና አርሶ አደር የንግድና የስራ መስህብ ነበራት፡፡ በባቡሩ ምክንያት ንግዱ የደራ ነው፤ የወረዳ ርዕሰ ከተማ እንደመሆኗ በአንድ ወይም በሌላ ምክንያት የሚመጣው ሰው ትንሽ አይደለም፡፡ ስለዚህም ከአፋሮች፤ ከአርጎቦች እና ከአረቦች በተጨማሪ ምንጃሬዎች (እንደ ግራዝማች መካሻ እና እትዬ አበበች)፤ ጠራዎች (እንደ እናቴ ሙላት እንግዳወርቅ) የመሳሰሉት መጥተው የኖሩባት ሆናለች፡፡

በኛ እድሜ ከትንሽ ተነስተው በራሳቸው ልፋትና ጥረት ሐብታም ሆነው፣ ዘመዶቻቸውን ከተማ አምጥተው አስተምረው፤ ለበርካታ ሌሎች ሰዎችም የስራ እድል ፈጥረው ተከብረውና ተወደው ፣ኖረው ካለፉት መሀል እትዬ አበበች አንዷ ናቸውና እስቲ የምናቀውን ያህል ስለ እሳቸው እንተርክ፤ ‘’እግረ መንገዳችንንም ሌሎችን እናነሳ እንጥል ይሆናል’’፡፡

ትውልዳቸው ምንጃር ነው፤ ታድያ በወጣትነታቸው ቆንጆ እንደመሆናቸው አንዱ የባንዳ ሹምባሽ ጠልፎ ጋራ ሙለታ ይወስዳቸዋል፡፡ ጊዜው የጠላት ዘመን እንደመሆኑ የባንዳ አለቆች ባለጊዜ ናቸውና ነው ይህ የሆነው፡፡ ሆኖም የኢጣልያንና የባንዳው ጀግንነት በሴቶቹ ላይ እንጂ በሸፈቱት አርበኞች ላይ አልነበረም፡፡ በዚያን ዘመንም ገና በወጣትነቱ እምቢኝ አልገዛም ብሎ የሸፈተ የአጎታቸው ልጅ የሆነ አቶ አፍራሳ የሚባል ዘመድ ነበራቸውና  ጋራ ሙለታ ወርዶ በጉልበት የተወሰዱትን ዘመዱን በጉልበት መልሶ ሀገራቸው አገባቸው፡፡

አበበች ባቡ ምንጃር ቢመለሱም በተጠለፉበት ወቅት ብዙ አይተው ብዙ ሰምተው ነበር፡፡ በመንገዳቸውም ስለ አዋሽ ከተማ ስለ ንግዱ ስለ ባቡሩ የሰሙት ሁሉ ማረካቸውና ልባቸው ሸፈተ፡፡ ሁለት እህቶቻቸውን ማለትም የነቲቸር በለጠን እናት ይናፍቁን  እና ይደነቃል ባቡን ይዘው አዋሽ ገቡ እድላቸውን ሊሞክሩ

የአባዎች ሙዚቃ

…Movie stars

find the end of the rainbow

with a fortune to win

It is so different from the world I am living in…

እንደሚለው እትዬ አበበችም ከባላገር የተዳፈነ ኑሮ ብርሐንና ሀብት ፍለጋ አዋሽ ገቡ፡፡ የእህታቸው ልጅ ደሞም አንደኛ ደረጃ አስተማሪዬ የነበረው ቲቸር በለጠ አንደነገረኝ ራሴም ከሌሎች እንደ ሰበሰብኩት ታሪካቸው የሚከተለውን ይመስላል፡፡

ከባለቤታቸው አንድ ወንድ ልጅ አላቸው ፡፡ በኃላ አዋሽ እንደገቡ አሁን መኖርያ ቤታቸው ባለበት ቦታ ላይ ያለች አንዲት አነስተኛ የጭቃ ቤት በሶስት ብር ተከራይተው የጠላ ንግድ ይከፍታሉ፡፡ እንደ ባለሙያነታቸው ጠላቸው ተወዳጅ ስለነበር ገበያቸው ቀላል አልነበረም፡፡ ገበያም ወጣ እያሉ ከአፋሮች ቅቤ እየገዙ በታኒካ ያስሞላሉ፡፡ ታኒካው በ 18 ብር ይሞላል፤ናዝሬት ይወሰድና ከ 30-35 ብር ይሸጣል፡፡ ትንሽ ጥሪት ሲቋጥሩ በአፈር ሰፈር ወደ ለገሀር መውጫው ላይ በኃላ አርጅተው ከሞቱት እማማ ጌጤ ከምንላቸው ሴትዮ ላይ ቦታ ይገዙና ቤት ሰርተው የጠጅ ንግድ ይጀምራሉ፡፡

ገበያው ሲደራ አንድ በአንድ ዘመዶቻቸውን ከምንጃር አዋሽ ያስመጣሉ፤መጀመርያ የመጡት አይናቸውን ያዝ ያደርጋቸው የነበሩትና በኃላም ጨርሶ የታወሩት እህታቸውን እና ልጆቻቸውን ረሱ እና በለጠ ግዛውን ነበር፡፡ ቲቸር በለጠ እትዬ አበበች አዋሽ እና ናዝሬት እስከ አስረኛ አስተምረውት ከዛም ሐረር መምህራን ማሰልጠኛ ተመርቆ የኛ ሁሉ አስተማሪ የነበረ ነው፡፡ የእንግሊዘኛውን Old Mcdonald had a farm የሚለውን መዝሙር

         ወንድሜ እርሻ አለው

         በጣም ጥሩ ነው

         በዚያ እርሻ በሬ አለው

         በጣም ጥሩ ነው

በዚያ እርሻ ላም አለው

በጣም ጥሩ ነው

         እዚህ እምቧ እዚያ እምቧ የትም እምቧ እምቧ

ብሎ በመተርጎም አስተምሮናል፡፡ ስለ ጠንቋይ አባይነት የሚያስረዳ ቲያትር ደርሶ ከወረዳ አስተዳዳሪው ጋር ተጣልቶ ነበር፡፡ የሱ ወንድም ረሱ ፈጣንና ኮሚክ ነበር፤ ልጅ ሆኖ እንደ ላሊበላ እየዘመረ ገንዘብና እንጀራ ይሰበስብና ጓደኞቹን ያበላል፡፡ እንደ ደረሳዎች እየዞየረ አረቦቹን ያስቃቸው ነበር፡፡ አንዲት ደከም ያለች ሴት በርሚል ስትገፋ ካየ ተቀብሎ እየገፋ ቤቷ ያደርሳል፡፡ አርጎባ ሰፈር እናቶች እንጨት ሲፈልጡ ካየ መጥረቢያውን ነጥቆ ይፈልጣል፡፡ ብቻ በትልቅ በትንሹ የተወደደ ነበር፡፡ ሲሞትም ትልቅ ትንሹ፤ ክርስቲያን እስላሙ በነቂስ ወጥቶ ቀበረው፡፡

ቀጥሎ ከጋራሙለታ ጠለፋ አስጥለው ያወጧቸውን ጋሽ አፍራሳንና ሁለት ሴት ልጆቻቸውን ማለትም በየነች አፍራሳን እንዲሁም የኔ እኩያ እና አብሮ አደጌን የውብነሽ አፍራሳን… ከዛ አበራሽን…. ቀስ በቀስ ሌሎችንም እያመጡ እያስተማሩ ማሳደግ ቀጠሉ፡፡

ሂደቱን እትዬ አበበች ብቻ ሳይሆኑ ሌሎችም ከ ቢየሁሉ እና ምንጃር የመጡ ሁሉ አድርገውታል፤ ግን የእትዬ አበበች በቁጥር ያይላል፡፡ የጠጅ ንግዳቸውን በአንድ በኩል እያካሄዱ በሌላ በኩል ከመኖርያ ቤታቸው አካባቢ ከነ ሰቃፍ ዑመር ቦታ እየገዙ ሰፊ ቦታ በመያዝ በጊዜው አስር አልቤርጎ የነበረውን ቡና ቤታቸውን ከፈቱ፡፡ በቀዳማዊ ኃይለስላሴ እና በደርግም የመጀመርያ አምስት አመታት ገደማ ቡና ቤታቸው በአዋሽ ከነበሩት ባለደረጃ ቡናቤቶች በቀዳሚነት ከሚመደቡት ነበር፡፡

ታታሪነታቸው እና በሳል አእምሯቸው ንግዳቸው እንዲስፋፋ ሀብታቸው እንዲጨምር ትልቁን አስተዋጽኦ አድርጓል፡፡ ከምንጃር አዋሽ ገብተው እየነገዱ ሲከብሩ አድማሳቸውን እንደብዙዎቹ ዘመነተኞቻቸው (ኮንቶምፖራሪስ) በአዋሽ ሳይገድቡ አንድ ልጃቸውን ለትምህርት ናዝሬት ልከው፤ እዛም ቤት ሰርተው ሌላ ቡና ቤት ከፈቱ፡፡ ስለዚህ አሁን ይዞታቸው አዋሽ ብቻ ሳይሆን ናዝሬትም ሆነ፡፡

ከገጠር አውጥተው ከተማ ካገቧቸው መሀል ስለ የአክስታቸው ልጅ ጋሽ አፍራሳ ትንሽ እናውጋላቸው እስቲ!

ጋሽ አፍራሳ በጠላት ጊዜ ገና ሰውነታቸው እንኳ በደንብ ሳይጠነክር በአካባቢው የጎበዝ አለቃ ስር ሆነው ተዋግተዋል፤ እልኸኛ እና ጀግና ሰው ነበሩ፡፡ በኃላም ሁለት ወንድ ልጆቻቸው በሳቸው ወጥተው ኢሕአዴግ ምንጃር ሲገባ ከሕወኃት ወታደሮች ሲዋጉ ሞተዋል፡፡ ጋሽ አፍራሳም እንድሜያቸው ሲገፋ ልጃቸው የውብነሽ ጋ እየተጦሩ ሲኖሩ ቁርባን አስቆርባቸዋለች፡፡ ታድያ የቁርባኑ ለት ከቤተክርስቲያን መልስ የውብነሽ አባቷን

‘’እንግዲህ አባዬ ከአሁን ወዲያ ሰው ቢናገርህም እንደበፊቱ በእልህ እየተቆጣህ መልስ መስጠት መጣላት የለብህም’’ ትላቸዋለች

         ‘’ለምን ቢሉ?’’

         ‘’እንዴ! ቆርበሀላ!’’

         ‘’እንዲህ ነኝና አፍራሳ! ታድያ የቆረብኩ እንደሆነ መጫወቻ ልሆን በጭራሽ!’’

ሰውነታቸው ነው እንጂ የደከመ ወኔያቸው አልነበረም፡፡ ወንድ ልጆቻቸው ብቻ ሳይሆን ሴቷ የውብነሽም እንዲሁ አትንኩኝ ባይ ኩሩ እና ቀጥተኛ ባህርይ ያላት ሰው ናት፡፡ እንግዲህ ልጅ ሆነን ቄስ አስተማሪ ማለት እንደ ጌታ ነው፡፡ እንኳን ቄስ አስተማሪ የመንግስት ት/ቤት ግብረገብ መምህር የነበሩት የኔታ ጽጌ እንኳ ተማሪዎችን በጎቻቸውን ማታ ማታ በረታቸው እንዲያስገቡላቸው ያስደርጉ ነበር፡፡ ታድያ አንድ ቀን መምሬ ማሞ የሚያስተምሯቸውን ልጆች ግቢያቸውን ያስጠርጋሉ፡፡ ከሚጠርጉት መካከል የአበራሽ ልጆች (የእትዬ አበበች የአክስት ልጅ የነበረች እና ቡና ቤቱ ውስጥ የነበረ በቡታ ጋዝ የሚሰራ ማቀዝቀዣ ፈንድቶ የገደላት) ይታክቱ፤ጸኃይ ፤አገኘሁ እና ማሙሽ ግቢውን ከሚጠርጉት መካከል ናቸው፡፡ የውብነሽ በአጋጣሚ በዚያ በኩል ስታልፍ ይህን ታያለች፡፡

         ‘’ገንዘብ ከፍለን አይደለ እንዴ የሚያስተምሩልን ለምንድነው እንደ አሽከር የምታሰሯቸው?’’

ብላ በመቆጣት ልጆቹን መንጭቃ ቤት ወስዳቸዋለች፡፡ ካደገች በኃላ በባህርይዋ ቀጥተኝነትና በጸባዩዋ የቡና ቤቱ ጠቅላላ አዛዥ አደረጓት፡፡ በደርግ የመጀመርያ አመታት ምድረ ካድሬ ሀብት አለው የተባለውን ሁሉ በሚያጠቃበት ወቅት የአዋሽ ባለ ጊዜዎችም እትዬ አበበችን ለማጥቃት ዳር ዳር ማለት ጀመሩ፡፡ ምንም ነገር ቢያጡባቸው

‘’የጸረ አብዮተኛ ኢዲዩ መሳርያ ይደብቃሉ፤ ገንዘብም ይልካሉ’’

በሚል ሊያስሯቸው አስበው የውብነሽን ያስሩና በሀሰትም ቢሆን እንድትመሰክርባቸው ግርፍ ይፈጽሙባታል፡፡ እሷ ግን ወንዶቹ እንኳን ከምንችለው በላይ ተቋቁማ አንድም ነገር ሳትወሻክት ከእስር የወጣች ጀግና ናት፡፡ ብዙ ወንዶች እንኳን ወፌላላ ግርፍ በጥፊ ብቻ ስንት ነገር ሲዘላብዱ የውብነሽ ግን በቆራጥነት ሁሉንም ተቋቁማ አልፋዋለች፡፡

እትዬ አበበችም የውብነሽን ስለመውደዳቸው ወሰን አልነበረውም

         ‘’ፊናንስ ሰፈር ቡና ቤት ልክፈትልሽ?’’

ብለዋት ነበር፤ ከየውብነሽ ተክለ ሰውነት (ፐርሰናሊቲ) ጋር የሚሄድ ስራ ስላልነበር አልተቀበለችውም፡፡ ይሁንና የውብነሽ ስታገባ በአዋሽ በኛ ጊዜ ድል ያለ ሰርግ ደግሰው ነበር የዳሯት፡፡ ምናልባት የአቡበከር ሰርግ ካልሆነ በስተቀር የየውብነሽን ሰርግ የመሰለ በዚያን ግዜ አላየንም፡፡

ወደ በኃላ እትዬ አበበች እጅግ ደርጅተው አንድ የስራ ፒክ አፕ ፔዦ 404 ሌላ የመጓጓዣ ፔዦ 505 ገዝተው በምቾትና በድሎት ኖረው ጊዜያቸው ሲደርስ አርፈው አዋሽ ደብረሳሌም ቅድስት ማርያም ቤተክርስትያን ቀብረናቸዋል፡፡

በእትዬ አበበች የተጠቀሙ ዘመዶቻቸው ብቻ አልነበሩም ከሰራተኞቻቸው ብዙዎቹን ኩለው ድረው ለወግ ለማዕረግ አብቅተዋል፡፡ ብዙዎች በሳቸው መኪኖች እጆቻቸውን አፍታትተው መንጃ ፈቃድ አውጥተው ራሳቸውን ችለውበታል፡፡ ናዝሬት ባለው በልጃቸው (ጋሽ ደምሴ) ቤትም ብዙ የአዋሽ ልጆች አርፈው ተምረውበታል፡፡

እነዚህ እንግዲህ በቀጥታ እትዬ አበበች ቤት ኖረው ተምረውም ሆነ ሰርተው ራሳቸውን የቻሉ ከሰላሳ በላይ ይሆናሉ በሞት ከተለዩት ጥቂቶች በስተቀር፡፡ ከነዚህም ውጪ በሳቸው ስር ተቀጥረው ሰርተው ተድረው ቤተሰብ የመሰረቱ ጥቂት አይደሉም፡፡ይህን ሁሉ ሀብት ያፈሩትና የዘመድ አዝማድ ዋርካ ሆነው የዘለቁት እትዬ አበበች ምንም ትምህርት ሳይኖራቸው ነው  የቄስ ትምህርት እንኳን አልነበራቸውም፡፡

ልክ አስራ ሁለት ሰአት ላይ ከመኖርያ ቤታቸው ተነስተው ድንክ ውሻቸውን አስከትለው ወደ ቡና ቤቱ ያመራሉ፡፡ እዛም ቡና ተፈልቶ እጣን ተጪሶ ሞቅ ሞቅ ብሎ ይጠብቃቸዋል፡፡ እስከ አንድ ሰዐት ወይም ከዚያ በላይ እዚያው ቡናው እየተጠጣ፣ ጨዋታ ደርቶ ሲጫወቱ፣ ትዕዛዝ ሲሰጡ፣ጥፋት ካዩ ሲገስጹ ይቆዩና ተነስተው ወደ መኖርያ ቤታቸው ይመለሳሉ፡፡ በዚህ መሀል ቡና ቤቱ በሰው ተመልቶ ይቆያል፡፡ እንዲሁ ግርማ ሞገሳቸው ብቻ የተለየ መስህብ ነበረው፡፡

ይህ ሲተረክ ቀላል ይመስላል ግን እትዬ አበበች የነበራቸው ግርማ፣ ተሰሚነትና ተወዳጅነት ዲካ/ወሰን አልነበረውም፡፡ እሳቸው ከሞቱ በኃላ ቡና ቤቱ  ግርማ ሞገሱን አጥቶ አሁን በድሮ ጥላው ብቻ የቀረ ሆኗል፡፡

የአዋሽ አድባር

ግራዝማች ሰይድ አሊ አቡበከር መደበኛ ሹመት ሳይኖራቸው በአዋሽ ዋና የአገር ሽማግሌ እና በብዙ ጉዳዮች በተለይም ጸጥታን እና የከተማ ቦታ ምደባን በተመለከተ አዛዥ ናዛዥ የነበሩ የከተማው አድባር ነበሩ፡፡ በተለይ በቀዳማዊ ኃይለስላሴ ዘመን፡፡ ቤታቸው ቢሆን ባለ አንድ ፎቅ ሆኖ ከፎቁ ፊት ለፊት ባለው ሰፊ በረንዳ ወንበር አስመጥተው በመቀመጥ ይፋዊ ያልሆነ ችሎት ያስችሉ ነበር፡፡ የባለጉዳዩ ብዛት ወረዳ ገዢው ግቢ ካለው አያንስም ነበር፡፡ ባህላዊ ጉዳዮች ሁሉ የሚታዩት በግራዝማች ሰይድ አሊ ችሎት ነበር፡፡በደርግ ጊዜም ቢሆን ጸጥታውንና የከተማ ቦታን ትተን የመጋላው ሰው ሌላ ሌላ ችግሩን የሚፈታው በሳቸው ችሎት ነበር፡፡

ልክ እንደ ሰይድ ሰቃፍ ሁሉ ግራዝማችም ስማቸው አሊ አቡበከር ሲሆን ሰይድ የማዕረግ ስማቸው ነው፡፡ ጃንሆይ በጣሊያን ጊዜ ከራስ አበበ አረጋይ ስር ሆነው ያደረጉትን ተጋድሎ እና ባንዲራ ከተመለሰ በኃላም አዋሽ አካባቢ ባሉት በአፋሮች ጉዳይ አስተርጓሚ እና ጉዳይ ፈጻሚ በመሆን ያደረጉትን ግልጋሎት ከግምት በማስገባት ይመስላል የግራዝማችነት ማዕረግ ሰጧቸው፡፡ ስለዚህ መንፈሳዊው ማዕረግ ሰይድ እና አለማዊው ማዕረግ ግራዝማች አንድ ላይ ቀላቅለን ግራዝማች ሰይድ አሊ እንላቸዋለን፡፡

አባታቸው አቡበከር ዋና ነጋዴ ነበሩ ከአልዩ አምባ ወሎን ይዞ እስከ አሰብ ግመል፣ ቅቤ፣ ከብት ይሸጡ ይለውጡ ነበር፡፡ ሶስት ልጆች ነበሯቸው፡፡ አሊ፣ዘይን እና አይደሩስ የሚባሉ፡፡ አይደሩስ በመካከለኛው አዋሽ ዘመናዊ የጥጥ እርሻ ከነበራቸው አረቦች አንዱ ሲሆን አሁንም አይደሩስ ካምፕ በመባል የሚታወቅ ካምፕ አለ፡፡ ዘይን አቡበከር በአዋሽ ነዋሪ ነበር፡፡ ግራዝማች አፋርኛ በደንብ በመቻላቸው በአፋር ጉዳይ ለጃንሆይ ሳይቀር አስተርጓሚ የነበሩት፡፡

ትንሽ የሚገርመኝ ነገር ግን፤ዘይንና አይደሩስ የሚታወቁት በስማቸው ሲሆን ሰይድ አሊ ግን የሰይድነትን ማዕረግ እንዴት ህብረተሰቡ እንደሰጣቸው ነው፡፡

ሰይድ አሊ አጠር ብለው ወፈር ያሉ የቀይ ዳማ ባለ ክብ ፊት ናቸው፡፡ ሰልካካ አፍንጫ፤ ትንንሽ ግን ጠልቀው የሚያዩ ቡናማ አይኖች ነበሯቸው፡፡ ጥርሰ ፍንጭት ሲሆኑ ሲቀመጡ እግራቸውን በስልት አጣምረው ነው፡፡

ግራዝማች የናጠጡ ሀብታም ነበሩ፡፡ ፊናንስ ሰፈር የጉምሩክ ጽ/ቤትና የንግስት ቡና ቤት የሳቸው ቤት ነበር፤ ክራዩ ጥሩ ስለነበር በደርግ ጊዜ ሲወረስ በወር የመጨረሻውን ክፍያ (250) ይከፈላቸው ነበር፡፡ ከሲቲዬ መቃሂ ፊት ለፊት የነበረው ትልቁ በረታቸው ሌላው የገቢ ምንጭ ነበር፡፡ በግመል አንድ ብር በከብት ሺልንግ በፍየልና በበግ ስሙኒ ይከፈልበታል፡፡ ብሩ በሳምንት ተጠራቅሞ ሲመጣ በስልቻ ተሞልቶ ነበር፡፡ የአዋሽ የመጀመርያ ወፍጮ ቤትም የሳቸው ነበር፡፡ የአካባቢው አፋሮች እንደ ባላባት ስለሚያዩዋቸው በየጊዜው የሚያመጡላቸውን ስፍር ቁጥር የሌለው ቅቤ በታኒካ እያሸጉ ለውጭና ለአገር ውስጥ ገበያ ያቀርባሉ፡፡ ከወረዳ አስተዳዳሪውም ሆነ ከማዘጋጃ ቤቱ ሹም ያልተናነሰ ስልጣን ስለነበራቸው ጉዳይ እያስፈጸሙ የሚያገኙት ገቢም ቀላል አልነበረም፡፡ ቦታ ተገዛ ተሸጠ ተለወጠ ማለት እሳቸው ጠቀም ያለ ገንዘብ አገኙ ማለት ነው፡፡ ማንንም እስረኛ ማስፈታት ይችሉ ነበር፡፡

ግራዝማች ደግም ነበሩ የተቸገረ መጥቶ ካለቀሰ ባዶ እጁን አይመለስም ነበር፡፡ በጣም ታማኝም ስለነበሩ ደርግ ከገባ በኃላም ቢሆን ሳዑዲ እና አዲስ አበባ ያሉ የየመን ከበርቴዎች የዘካ ገንዘብ ለሚያስፈልጋቸው እንዲያከፋፍሉ የሚሰጡት ለሳቸው ነበር፡፡

በከተማው ችግርም ተካፋይ ናቸው፡፡ የሰብለወንጌል ት/ቤት የእረፍት ቀን እሑድና ሰኞ እንዲሆን ያስደረጉ እሳቸው ነበሩ፡፡ ተማሪዎች በገበያው ቀን ቤተሰቦቻቸውን እንዲረዱ ለራሳቸውም ገንዘብ እንዲያገኙ ተብሎ፡፡

የተጣሉ ሰዎች በተለይም አርጎባ አፋርና አረቦች ፍ/ቤት ከመሄድ ግራዝማች ችሎት ቀርበው መዳኘትን ይመርጣሉ፡፡

ባለቤታቸው እመት ሲቲ ቀደም ሲል የቃሲም አፎይኔ (ባለ ትልቅ አፍ) ባለቤት ነበሩ፡፡ ግራዝማች ስለወደዷቸው ጠልፈው ነበር ያገቧቸው፡፡ ሴትዮዋ ሾተላይ ነበረባቸው፤ ከቃሲም ብዙ ግዜ አርግዘው ምጣቸው የሞት ያህል ነበር የሚያሰቃያቸው፡፡ ሲወለድም የሞተ ይሆናል ወይም ይሞታል፡፡ ግራዝማች ግን ስለወደዷቸው ጠለፏቸው፡፡ ቃሲም ኃይለኛ ስለነበር ጠብ ያነሳል ተብሎ ተገምቶ ነበር፡፡ እሱ ግን

‘’ገላገለኝ አቦ! ባረገዘች ቁጥር ስቃዬን ነበር የማይ’’ ብሎ ነገሩን ተወው፡፡ ግራዝማች ያላቸውን ስልጣን አመዛዝኖም ይሆናል፡፡ እሜት ሲቲ ከግራዝማች አቡበከርን ብቻ ነው የወለዱት፡፡ እሱንም በደንብ ነበር ያሳደጉት፡፡ በጊዜው ማትሪክን በጥሶ አለማያ ኮሌጅ የገባ ብቸኛ የአዋሽ ልጅ ነበር፡፡

ሰይድ አሊ አንድ አጭር መትየስ ነበራቸው (ከፊሻሌ ሽጉጣቸው ሌላ)፡፡ በደርግ ጊዜ ካድሬዎች መጥተው በወሬ የሰሙትን ጠየቋቸው

‘’መትረየስ አለዎት አሉ፤ያስረክቡን?’’ ብለው ይጠይቋቸዋል፡፡

‘’አዎን አለኝ ሰሜን ሸዋ ከራስ አበበ አረጋይ ጋር በሽፍትነት ዘመኔ ከጣልያን የማረክሁት ነው፡፡ ጠላትን ነው የተዋጋሁበት፡፡ አሁንም እናንተ ለሀገር ጠላት መግደያ ከፈለጋችሁት ውሰዱት’’ አሏቸው፡፡ አመስግነው ተዉላቸው፡፡

የግራዝማች ችሎት

ቀደም ሲል ጠዋት ነበር ችሎት የሚቀመጡት፡፡ እንግዲህ ችሎት እንበለው እንጂ መደበኛ ችሎት አይደለም፡፡ ሁሌ ጠዋት ማዘጋጃ ይሄዳሉ፤ ጉዳይ ኖራቸውም አልኖራቸውም፡፡ ከዚያ ምንም ነገር ከሌለ ወደ አምስት ሰአት ቤት ሲመጡ ባለጉዳዮች ካሉ ፎቃቸው ላይ ይወጡና ያነጋግራሉ፡፡ ይህንን ነው ችሎት ያልነው፡፡ ብዙ ጉዳዮች ማህበራዊም፣ ህጋዊም ሆነ ምጣኔ ሀብታዊ ጉዳዮች ይታያሉ በችሎቱ፡፡ ተበድያሁ የሚል በዳዩን ይከሳል፤ ግራዝማች ጉዳዩን ሰምተው አንዳንዴ እዚያው አንዳንዴ ሌላ ቀን ተመለስ ይሉና የሚመስሏቸውን አነጋግረው ጉዳዩን አጥንተው ይወስናሉ፡፡ የተጣላ ይታረቃል (አንዳንዴ ያልተጣላም ይጣላል)፤ የቸገረው ፈረንካ ይቸረዋል፤ በቢሮዎቹ ጉዳይ ያለበት መታያ ይከፍላል፡፡ ከአንዱ ይቀበላሉ ለሌላው ይሰጣሉ፡፡ መቸም ከተቀበሉት የሚሰጡት ማነሱ እንዳለ ሆኖ፡፡

አፋሮች የከተማውን ሰው ሲገድሉ በማጣራቱ፣ ገዳዩን ፈር በማስያዙ፣ ጉዳዩን ከተቻለ በጉማ በማስጨረስ የግራዝማች ሚና ከፍተኛ ነው፡፡ ዛሬ ዛሬ እንኳን ትተዋል ያኔ አፋሮች የከተማ ሰውን ባጋጣሚ ወጣ ብሎ ካገኙት ይገድሉና ሰልበው ይሰወራሉ፡፡  አላማቸው ሁለት ነው አንደኛ የከተማ ሰው ሁሉ ክርስቲያን ይመስላቸዋል ስለዚህም ካፊር መግደል ጀነት ያስገባል ብለው ያምናሉ፡፡ ሁለተኛ የሰለቡትን ሰው ብልት ወስደው በማሳየት እየፎከሩ ወንድነታቸውን(ጀግንነታቸውን) ያስመሰክራሉ፡፡

በዚህም የተነሳ ከከተማው ትንሽ ወጣ ከተባለ አደጋ ነበረው፤በተለይ እንጨት ለቃሚዎችና ድንጋይ አውጪዎች ከከተማው ውጪ ስለሚታትሩ ኢላማዎቻቸው ነበሩ፡፡ በከተማውም ቢሆን ከአራት ሰዓት በኃላ እንደ ሰዓት እላፊ አይነት ነገር ነበር፡፡ ከአገር ግዛት ግቢ ደወል ይደወላል ከዚያ በኃላ ለገሀር ካልሆነ በስተቀር ሌላው ከተማ እርጭ ይል ነበር፡፡ ወደ በኃላ ግን ይሄ እየተቀየረ ሄዷል፡፡

የከተማው የእሰላም ሰፈር ጉዳዮች (ፍጥምጥም፣ሰርግ፣ህመም፣ሞትና የመሳሰሉት) ይነሳሉ ይጣላሉ በችሎቱ፡፡ በርካታ አፋሮች ከዚህ ችሎት አይታጡም፡፡

ለማንኛውም ግን አፋሮች ከመንግስት መስሪያ ቤት የሚያገናኝ ጉዳይ ካላቸው ዋናው አስፈጻሚያቸው ግራዝማች ነበሩ፡፡

በኃላ በኃላ ደርግ መጥቶ ስልጣናቸው ሲቀንስ ችሎቱ ወደ ከሰዓት በኃላ ተቀየረ፡፡ ወደ 10፡30 ገደማ ላይ ከሐጂ ሙክታር ቤት ፊት ለፊት ካለው ትልቅ ዋርካ ስር ይሰየማሉ ግራዝማች ፡፡ እግራቸውን አነባብረው የሚቀመጧት ቄንጠኛ አቀማመጥ ነበራቸው፡፡ ከዚያ ሰዉ ቀስ በቀስ ይመጣል፤ ጨዋታው ይሞቃል፡፡ በጨዋታው መካከል አንዳንድ ማህበራዊና ምጣኔ ሀብታዊ ነገሮችም ይነሳሉ ይወሰናሉም፡፡ ለአማላጅነት ይጠየቃሉ፣ በአንዳንድ ጉዳዮች ምክራቸው ይጠየቃል፣በሌሎች ጉዳዮች ደሞ እርዳታቸውን፡፡

ባለቤታቸው እሜት ሲቲም የአረብና አርጎባ ሴቶች የበላይ ነበሩ፡፡ የአርጎባ እና የአረብ ሴቶች ገንዘብ ሲቸግራቸው እሳቸው ጋ መጥተው ወርቅ አስይዘው ገንዘብ ይበደራሉ፡፡ ገንዘቡ ከተመለሰ ወርቁም ይመለሳል ካለሆነ…

ሲሞቱ ለአንድ ልጃቸው አቡበከር ከአምስት ኪሎ በላይ ወርቅ አውርሰውታል፡፡ አቶ ከበደ ተክሌ እንደነገረኝ ከሆነ

‘’እኔ ራሴ በትልቅ የማስታጠቢያ ሳህን ሙሉ ወርቁን ሲያስረክቡት እማኝ ነበርኩ’’ ብሎኛል፡፡

 እሜት ሲቲ ከናቴ ጋር በጣም ቅርበት ነበራቸው፤እናቴ ለእስላም ዓመት በአሎች ፍየል ገዝታ ትልክላቸዋለች እሳቸውም ለኛ ፋሲካ ሁለት ወይም ሶስት ዶሮች ከአስራሁለት እንቁላሎች ጋር ይልካሉ፡፡ ልጅ ሆኜ እናቴን ተከትዬ ቤታቸው እሄድ ነበር፡፡ ለረዢም ሰዓታት ባለማቋረጥ ይጫወታሉ፡፡ እናቴ ልትሄድ ስትል በር ድረስ ይሸኟትና እንደገና በሩ ላይ ሰፊ ወሬ ያወራሉ፡፡ ያኔ ታድያ እነሱ አውርተው እስኪጨርሱ መጠበቁ ያሰለቸኝ ነበር፡፡ አሁን ደሞ ያንን ሁሉ ሰዓት ምን ያወሩ እንደ ነበር ይገርመኛል፡፡

አንዴ መጋላ በላይ ወደ መስጊድ በሚወስደው ዘቅጡጣ በኩል ስሄድ እሳቸው በአግድመቱ ሙስባሀቸውን እየቆጠሩ ይሄዳሉ፡፡ አባይ ደሴ የምትባል አንዲት ወፍራም ደሀ ሴትዮ ነበረች እና አግኝታቸው

‘’የአቡበከር እናት ደህና ዋልሽ?’’

‘’አልሀምዱሉላሂ አንቺስ’’

‘’ደህና ነኝ፣ የምልሽ- ሙስባሂሺን በመንገድም አትተዩውም?

‘’አላህን እየለምኩ ነዋ!’’

‘’አንቺ ደሞ ምን አጣሽና ነው አላህን የምታስቸግሪው፤እንዴ? እናንተም ከለመናችሁ እኛን ድሆቹን እንዴት ይስማን? ለምን ትሻሚናለሽ?’’ አሏቸው

‘’አይ እኔስ ምንም አላጣሁ አልሀምድልላሂ እንዲያው ብቻ ሙላትን ቢያሰልምልኝ ብዬ ነው’’ ሲሏት ክው ብዬ ደነገጥሁ፡፡ በልጅነት አእምሮዬ ተረብሼ ነበርና እናቴን ነገሩን አስረድቻት እንድትጠነቀቅ ነግሬያት ነበር፡፡

እንግዲህ ያኔ እንዲህ ሙስሊምና ክርስትያን ተዋዶ ተፋቅሮ መኖር ይችል ነበር፡፡ ለሙስሊማን የወደዱት ሰው እንዲያገኝ የሚፈልጉት ትልቅ ነገር እስላምነትን ስለሆነ ነው ለእናቴ ያንን የተመኙላት፡፡

የአቡበከር እናትን ስናነሳ እሕትየው እሜት ሞሚናን ሳላነሳ ማለፍ ትልቅ ግድፈት ይሆናል፡፡ እሜት ሞሚና የሚታወቁት በትልቅ መቀመጫቸው ነበር፡፡ ከዚያ በፊትም ሆነ በኃላ እንደ እሜት ሞሚና አይነት መቀመጫ አይቼ አላቅም፡፡ ትልቅነት ብቻ ሳይሆን በሚሄዱበት ጊዜ የራሱ ልዩ እንቅስቃሴ ነበረው፡፡ ሁለቱ መንታ መቀመጫዎቻቸው የየራሳቸው እንቅስቃሴ አላቸው፡፡ እዛው ያደግነው እንኳን እሜት ሞሚና ሲሄዱ የምንሰራውን ወይም መንገዳችንን አቁመን ለላንቲካ ነበር የምናያቸው፡፡ የማያቃቸውማ ሲሆን ገምቱት፡፡

ታድያ እሜት ሞሚና ብዙ ልጆች ቢኖሯቸውም እኔ በጣም የማስታውሰው አሊ አብዶን፤ ማለት ትንሽ ልጃቸውን ነበር፡፡ አንዴ ናዝሬት ይዟቸው አብረው ሲሄድ የናዝሪት ማቲዎች ከማርስ ድንገት ዱብ ያለ አረንጓዴ ፍጡር ያዩ ይመስል እናቱ ላይ ሲያፈጡ አሊ አብዶ

‘‘ምን አባትህ ይገትርሃል?ጢዝ አይተህ አታውቅም?’’

እያለ ከአላፊ አግዳሚው ጋር ሲጣላ ነበር አሉ፡፡ አንዴ ደሞ መጋላ በርሜል ላይ ተቀምጠን ወሬ ስንቆምር እትዬ አበበች ባቡ ባጠገባችን ያልፋሉ፡፡ እሳቸውም ራቅ እንዳሉ አንደኛው

‘‘ልጆች ከወ/ሮ አበበች እና  ከሞሚና መቀመጫ የትኛው ይበልጣል?’’ ብሎ ሲጠይቅ አሊ አብዶ እዚያው ስለነበር ጠብ ይነሳል ብለን ደነገጥን፡፡ አሊ አብዶ ግን ትንሽ አሰብ አደረገና

‘‘ሊሻን አበበች ባቡ መዓ ፍሉስ አባለሃ፤ ላኪን ኡማ ሀቂ ኪዳ ጠፈጠፈሀ’’ ሲል ሁላችንም በሳቅ ፈረስን

‘‘አበበች ባቡን ከገንዘብ ጋር ነው  የሰጣት፤ የኔን እናት ግን ዝም ብሎ ነው የጠፈጠፈባት’’

እንደማለት ነው፡፡ ብዙ ግዜ በትንሽ ነገር ከሰው የሚጣላው አሊ አብዶ ጓደኞቹ ስለ እናቱ ሲፈትሉበት የነበረው ትዕግስት ይገርመኝ ነበር፡፡ ሌላ ጊዜ በርጫ ላይ ለመቃም እየተሰናዳን እያለ አንድ የአሊ አብዶ ጓደኛ ከመስጊድ ይመጣል፡፡ እንግዲህ እስላሞች ከመስገዳቸው በፊት ይተጣጠባሉ፡፡

‘‘ስሙ! ዛሬ መስጊድ ኡዱ ስናረግ የእሜት ሞሚናን ባል ብልት አየሁት ይሄን ያህላል’’ ብሎ የእጁን መዳፍ አሳይን፡፡ ቁጭ ብሎ ይከዝን የነበረው አሊ አብዶ ተወርውሮ አነቀው ስል ረጋ ብሎ

‘‘ይሄን አከለ (መዳፉን እያሳየ) ወላ ይህን (ክንዱን እያሳየ) የምትችለው ሞሚና አንተ ምን ፈደለህ?’’ ብሎ ነገሩን አለፈው እኛም ሳቅን፡፡

አዲስ አበባ እናቱን ይዞ የያኔ ሴይቸንቶዎችን ያስቆምና

‘’ሁለት ሰው መርካቶ’’

ሲል ስቀውበት ነበር የሚያልፉት፡፡ የኃላውን መቀመጫ ብቻቸውን ካላስያዛቸው ሌላ ሰው መቀመጥ ስለማይችል ነው፡፡

ግራዝማች ቀስ በቀስ እያመማቸውና እየደከሙ ሲመጡ የከተማው ዋና ዋና አረብ፤ አርጎባ እና አፋሮች ፎቃቸው ላይ ይፈረሽላቸውና ከቀኑ ስምንት ሰአት እስከ አስራ ሁለት ሰአት ሲያጫውቷው ይውላሉ፡፡ እንደዚያ ደክመው እንኳ ተወዳጅነታቸውና ተሰሚነታቸው አልቀነሰም ነበር፡፡

Add post to Blinklist Add post to Blogmarks Add post to del.icio.us Digg this! Add post to My Web 2.0 Add post to Newsvine Add post to Reddit Add post to Simpy Who's linking to this post?

የ አይ ቲ አጭር ታሪክ 28 Feb 4:02 AM (14 days ago)

ይህ መጣጥፍ ስለ የመረጃ ቴክኖሎጂን (INFORMATION TECHNOLOGY) (IT)ምንነት፣ እድገት እና አሁን ያለበትን ደረጃ ከአንድ ጸኃፊ አረዳድ አንጻር ለማስቀመጥ የሚሞክር ጥረት ነው፡፡ ታዋቂው እስራኤላዊ የታሪክ ምሁር ዩቫል ኖሕ ሐራሪ 2024 ኔክሰስ በሚል ርዕስ አንድ መጽሐፍ አሳትሟል፡፡ ይህ ጸኃፊ ቀደም ሲል ሳፒያን በተኘውና በአለም አካባቢ በዘጠኝ ቋንቋዎች ተተርጉሞ ከ45 ሚሊዮን በላይ ቅጂ የተሸጠው መጽኃፍ ደራሲ ነው፡፡ ለአንድ ኢ-ልብወለድ መጽኃፍ ይህን ያህል አንባቢ ማግኘት ቀላል ነገር አይደለም፡፡

መጽኃፉን በማንበብ ላይ እያለሁ እና አንብቤም ከጨረስኩ በኃላ ፍሬ ሀሳቡን በምጥን ይዘት በአማርኛ ለማቅረብ እየሞከርኩ ነበር፡፡ ወደ በኃላ ግን ሳስበው ይህ ከሚሆን ራሱ ደራሲው የጻፈውን አሳጥሮ እና ቀለል አድርጎ በአማርኛ ማቅረቡ የተሻለ ስለመሰለኝ ይህንኑ አደረግሁ፡፡ በብዛት እንኳ የተለመደው እንደዚህ አይነት እጅግ ጠቃሚ የሆነ መጽኃፍ ሲወጣ ለመጽኄት እንዲሆን በጣም አጠር አድርጎ ማቅረብ ነው፡፡

ለኢትዮጵያውያን አንባቢዎች ግን ከዚህ ይልቅ የራስ መግቢያና አስተያየት ተጨምሮበት ዋና ዋና ይዘቶችን ብቻ ማቅረቡ …

አንደኛ በአጠቃላይ የማንበብ በተለይ ደሞ ኢ-ልቦለዳዊ መጻህፍትን የማንበብ ልምድ ባልዳበረበረት

ሁለተኛ በይነ-መረብ (ኢንተርኔት) እና ማህበረሰባዊ መገናኛ ብዙሀን የህዝቡን ቀልብ በያዘበት ሁኔታ

መጣጥፉ አጥሮ፣ቀለል ብሎና አዝናኝ በሆኑ ሰዋዊ ወይም ግላዊ ትርክት (anecdot) ተቀናብሮ መቅረቡ ተነባቢነቱን ይጨምረዋል በሚል እምነትና ተስፋ በዚህ መልኩ ቀርቧል፡፡ ይህም ሲሆን በመጣጥፉ ያሉት የዋና ዋና ጽንሰ ሀሳቦች ትርጉም በቀጥታ የሀራሪ (ደራሲው) መሆናቸው ይሰመርበት፡፡

ዩቫል ኖህ ሀራሪ

ክፍል አንድ

ምዕራፍ አንድ

በአንድ ኢ-ልቦለዳዊ ጽሁፍ ከሁሉም በፊት የጽሁፉን ዋና ዋና ጽንሰ ሐሳቦችን ትርጉም ማስቀመጡ እጅግ ጠቃሚ ነው፡፡ ስለዚህም ሀራሪ መረጃ (ኢንፎርሜሽን) የሚለውን ቃል በመጽሀፉ የተጠቀመበት በምን እሳቤ ነው?

መረጃ የአመለካከት ጉዳይ ነው፣ይላል ሀራሪ፡፡ ቀጠል ያደርግናም በቀጥታ መረጃ ማለት ይህ ነው ከማለት ይልቅ እንደ መረጃ ማንነት የተወሰዱ ግን መረጃ ያልሆኑ ሀሳቦችን ይዘረዝራል፡፡ለምሳሌም መረጃ የኅላዌ ወይም የዕውነታ ነጸብራቅ  ስለሆነ ዕውነታ (ትሩዝ) ነው የሚለውን ሀሳብ እንደማይቀበል ያስቀምጣል፡፡

በደራሲው እምነት ማንኛውም ነገር ለምሳሌ ኮከብ፣መጋረጃ፣ ወይም ወፍ በትክክለኛው አውድ ከተገኙ መረጃዎች ናቸው፡፡

የበዙት መረጃዎች ምንም ነገርን አይወክሉም፡፡ ስለዚህ ዕውነትንም አይወክሉም፡፡ በመሰረቱ እውነት የሚባለው የአንድ ዕውነታ ከፊል ገጽታን እንድናተኩርበት ሌላውን ደሞ የምንዘነጋበት አካሄድ ነው፡፡ ያ ከፊል ገጽታ ነው እውነታ፡፡

እዚህ ላይ የራሴን ልምድ ብጨምር፡፡ ለምሳሌ አንድ ሰው ለጋስ ሰው ነው ስንል ያ ሰው ሁልግዜ ለሁሉም ሰው ለጋስ ነው ማለት አይደለም፡፡ ሰውየው ብዙውን ግዜ ለብዙ ሰዎች ለጋስ ሲሆን አንዳንድ ግዜ ለአንዳንድ ሰዎች ንፉግ ነው፡፡ ግን ካጠቃላይ ሰውነቱ የጎላውን ገጽታ እንደ ሙሉ ባህርይ እንወስድና እከሌ ደግ ነው ብለን እንደመድማለን፡፡

ይህ ለግለሰብም፣ለኅብረተሰብም፣ለክስተቶችም ይሰራል፡፡ ለምሳሌ አይሁዶች ገብጋባ ናቸው ሲባል እሰማለሁ፣ ከዚህ ጋር ተያይዞም አንዳንድ ቀልዶች ይነገራሉ፡፡ አንድ በጣም ቸር የሆነች ጀርመናዊ ታማ ብዙ ደም ያስፈልጋታል፡፡ ነገሩን የሰማው ጎረቤቷ አይሁዳዊ አንድ መቶ ማርክ ከከፈለችው የሚያስፈልጋትን ደም ሊሰጣት ቃል ይገባላታል፡፡ በዚያም መሰረት ሴትየዋ ደም ካገኘች በኃላ ድና ቤቷ በገባች በነጋታው አይሁዱ መቶ ማርኩን እንድትሰጠው ይጠይቃታል፡፡ ያች እንኳን ለራሷ ለሌላውም ቸር የነበረች ሴትዮ ምክንያት እየፈጠረች ታመላልሰው ጀመር፡፡

አይሁዱም ነገሩ ስለጠነከረበት እሱንም ሴትየዋንም የሚያውቁ ሽማግሌዎችን ‘‘መቶ ማርኬን ከለከለችኝ’’ ብሎ ቢያማክር አንዱ፣

‘’ሴትየዋ ንፉግ አይደለችም፣ እንዴት ከለከለችህ? ለመሆኑ መቶ ማርኩን መቼ ነው ያበደርካት?’ ብሎ ይጠይዋል፡፡ የአይሁድ ነገር ትናንት አበድሮ ዛሬ ውለጂ ብሏት እንደሆነ በመገመት፡፡

‘’አበድሬያት አይደለም ታማ ደም አስፈልጓት በነፍሷ ደርሼ ደሜን ነጥቻት ነው፡፡ በምትኩ  መቶ ማርክ ልትሰጠኝ ተስማምታ ነበር፡፡ መቸም ታሞ የተነሳ እግዚአብሔርን ረሳ አይደል የሚባለው ይኸው አሁን ነገ ተነገወዲያ እያለች ከለከለችኝ’’ አለ አይሁዱ፡፡

‘‘አዪ በዚህ ጉዳይ እንኳ አንገባም፡፡ አሁንኮ እሷ ያላት የአይሁድ ደም ነው፡፡ እንዴት ብላ ነው መቶ ማርክ ባንዴ ላጥ አርጋ የምትሰጥህ፡፡ ይሄን ቀደም ብለህ ደምህን ስትሰጣት መገመት ነበረብህ’’

ብለው አሰናበቱት፡፡

እዚህ ላይ ምናልባት ብዙ አይሁዶች ብዙውን ግዜ ገንዘብ ከማውጣታቸው በፊት የበዛ ጥንቃቄ ያደርጉ ይሆናል፡፡ ይህን ከፊል እውነታ ሙሉ አድርጎ ሁሉንም አይሁድ አባሀና ማድረጉ እውነታን በትክክል መወከል አይሆንም፡፡

አንግዲህ ሀራሪ የሚለው ምንድነው መረጃ የተለያዩ ነገሮችን አንድ ላይ በመቋጠር አንድ አዲስ እውነታን ይፈጥራል፡፡ አንድ ወንድ ና ሴትን አጣምሮ ትዳርን ከአንድ በላይ የሆኑ የተለያዩ ነገዶችን አያይዞ ሀገርን ይፈጥራል፡፡ ስለዚህም ዋና ባህርዩ የተለያዩ አካላትን (entity) አገናኝቶ አንድ መረብ (network) ያቆማል፡፡ ስለዚህ ዋና ባህርዩ ማያያዝ (connection) እንጂ ውከላ (representation) አይደለም፡፡ መረጃ ነገሮችን መመስረት ነው ወይም ነገሮችን በአንድ መልክ እንዲመሰረቱ ማድረግ፡፡

ለምሳሌ ኮከብ ቆጠራ ፍቅረኞችን ይወክላቸዋል በሚላቸው ከዋክብት መሰረት በፍቅር ያዋህዷቸዋል፡፡ ፕሮፓጋንዳ የተለያዩ ሰዎችን በአንድ ፓርቲ ያደራጃቸዋል፣ የማርሽ ሙዚቃ የወታደሮችን ሰልፍ ይመሰርታል፡፡

ስለዚህም መረጃ የተለያዩ ነገሮችን አያይዞ አዲስ በይነ-መረብ መፍጠር ነው፡፡ በዚህ ሂደት መረጃ ሰዎችን በእውነት ላይ በተመረሰተ ክስተት ሊያገናኝ ይችላል፡፡ በዚህም እውነትን ወከለ ማለት እንችላለን፡፡ ለምሳሌ በኦገስት 1969 ከመቶ ሚሊዮን በላይ ሰዎች በቴሌቪዥን ፊት ለፊት ተቀምጠው ኒል አርምስትሮንግ ጨረቃ ሳይ ሲራመድ ተመልክተዋል፡፡ የዛ ትርዒት ይዘት እውነታ ነበር፡፡

በሌላ በኩል ግን የዘረመል መረጃ (ጄኔቲክስ ኢንፎርሽን) በተፈጥሮ ሂደት እልፍ አዕላፍ ሴሎችን ሲየቀናጅ ወይም የሙዚቃ ኖታ በሺ የሚቆጠሩ ሰዎችን ሲያስደንስ መረጃው እውነታን በትክክልም ሆነ በስህተትም አቀናጀ አንልም፣ አቀናጀ (connect) ብቻ እንጂ፡፡

እዚህ ላይ የተሳሳተ መረጃ (mis information) እና የተዛባ መረጃን መለየት ጠቃሚ ነው፡፡ ለምሳሌ ኮከብ ቆጣሪዎች በከዋክብት ምልክት ሰጪነት አምነው ፍቅረኞችን ‘’ኮከባችሁ ግጥም ስለሆነ ብትጋቡ ጥሩ ነው’’ ሲሉ የተሳሳተ መረጃ ነው የሰጡት ግን አውቀው ፍቅረኞቹን ለማታለል ሲሆን የሁለቱ ሰዎች ኮከቦች ቢዋሃዱ ውጤታማ ናቸው ብለው ስላመኑ፣ በተሳሳተ እውቀት የተሰጠ መረጃ ስለሆነ የተዛባ መረጃ እንለዋለን፡፡

በሌላ በኩል አክራሪ ሁቱዎች በ ሬድዮ    ቱትሲዎች የተረገሙ በረሮዎች ስለሆኑ ፍጇቸው በማለት ሲቀሰቅሱ በተሳሳተ መረጃ (disinformation) የዘር ፍጅት አስፈጽመዋል፡፡

መረጃ የተለያዩ ነጥቦችን በአንድ በይነመረብ (network) አያይዞ አዲስ እውነታን መፍጠር ነው፡፡

መረጃ በሰው ልጅ ታሪክ ውስጥ

መረጃ አንዳንዴ እውነታን ቢያመለክትም ሌላ ጊዜ ደሞ ከዚህ በተቃራኒ እናገኘዋለን፡፡ ሁሌም ግን ያገናኛል ወይም ትስስር ይፈጥራል፡፡ ምንም እንኳ ያገኘነው መረጃ ምን ያህል እውነታን ይወክላል ብለን መጠየቁ አግባብ ቢሆንም፣ መረጃ በሰው ልጅ ታሪክ ውስጥ ሚጫወተው ሚና ይበልጥ ግልጽ የሚሆንልን – እንዴት አድርጎ ሰውን ከሰው አገናኘ፣ በዚህ ሂደትስ ምን አይነት አዲስ የትስስር መረብ ፈጠረ? ብለን ስናጠናው ነው፡፡

ምክንያቱም የትስስር መረብ መፍጠር ወይም ማገናኘት የመረጃ ዋናው ባሕርይ ስለሆነ፡፡

ተመልከቱ እንግዲህ ብዙ መረጃ ባገኘን ቁጥር ይበልጥ ወደ እውነታ እየቀረብን እንመጣለን የሚለው የየዋሆች አስተያየት የተሳሳተ የሚሆነው ስለዚህ ነው፡፡ የመረጃ ብዛት ብቻውን እውነታን አያመለክትም፡፡ የናዚዎች የፕሮፓጋንዳ አለቃ ዮሴፍ ጎብልስ ‘‘አንድን ሐሰት ደጋግሞ በመናገር እውነት ማድረግ ይቻላል’’ የሚለው በመረጃ ብዛት የሌለ እውነታ መፍጠር እንደሚቻል ለማሳየት ነው፡፡

በኛ በሐበሾች ልምድ ብንሄድ

‘‘ይህን ነገር ከየት ሰማኸው?’’ ተብሎ ሲጠየቅ

‘‘እንዴ ! ይኸማ ሁሉም የሚያወራው እኮ ነው’’ የሚለው መልስ ሁል ግዜ ትክክል አይሆንም፡፡

ከድንጋይ ዳቦ ዘመን አንስቶ እስከዛሬው የመረጃ ቴክኖሎጂ ወቅት በርካታ በእውነታም ሆነ በጥበብ/ጥልቅነት ላይ ያልቆሙ ግንኙነቶችን እናገኛለን፡፡ የሰው ዘር አለምን ለመግዛት የበቃው መረጃዎችን ሁሉ ወደ እውነታ በመቀየሩ ሳይሆን ብዙ ሰዎችን አገናኝቶ እና አስተሳስሮ ችግሩን ለመፍታትም ሆነ ኑሮውን ለማሸነፍ ስለቻለ ነው፡፡

ግዙፍ እንስሳትን ለማደንም ሆነ በፋብሪካ ምርትን ለማግኘት የበርካታ ሰዎች ትብብር/ቅንጅት ወሳኝ ነው፡፡

የሰው ዘር ኑሮውን ለማሸነፍና አለምን ለመግዛት በመጀመርያ ስራ ላይ ያዋለው የመረጃ ቴክኖሎጂ መጠርያ ታሪክ/ተረት (story) ይባላል)፡፡ በምዕራፍ ሁለት ታሪክ/ተረትን በሰፊው እንመለከታለን፡፡

ምዕራፍ ሁለት

ትርክቶች፣ ገደብ የለሽ  ግንኙነቶች ወይም ትስስሮች

Stories: Unlimited Conecctions

በዚህ መጣጥፍ ላይ ስቶሪ የሚለውን ቃል ታሪክ/ትውስት/ትርክት እያልን በማቀያየር እንጠቀምበታለን፡፡

የተለያዩ ቤተሰብ አባላትን ለማስተባበር ያስቻለው ዝግመታዊ ለውጥ የመጣው ሰዎች የመናገርና ቋንቋ ችሎታቸውን እያዳበሩ በመምጣቻው ነው፡፡ አደን ከአንድ በላይ የሆኑ ሰዎችን ትብብር የግድ ስለሚል ይህም ግዴታ ሰዎች የመናገር ክህሎታቸውን እያዳበሩ እንዲሄዱ ወሳኝ ሚና ተጫውቷል፡፡

አንድ ቤተሰብ ብቻውን ለማደን ቢችል እንኳ ሁሌ ውጤታማ አይሆንም፡፡ በስንት ትብብርና ጥረት አውሬውን ቢገድል እንኳ፣ የገለደውን አውሬ ሊቀማው የሚመጣውን አንበሳም ሆነ ነብር ለመቋቋም መተባበርና ይህንንም ትብብር ለማሳለጥ በጎሣ መረብ (tribal network) ግንኙነቱን ማደራጀት ነበረበት፡፡

ይህ በሰዎችና-ሰዎች ያለ ግንኙነት ጥንካሬ እና ዘለቄታ እንዲኖረው ጎሣውን ሊያሰተባብር የሚያስችል ትርክቶች ቀስ በቀስ እየዳበሩ ሄዱ፡፡ የአያት ቅድመ-አያቶችን ገድል እና ከሌሎች ጎሣዎች ጋር በሚኖረው ትግል የፈጸሙትን ገድል በማስዋብ እና በማራቀቅ ትርክቶች ዋና የመረጃ ቴክኖሎጂ ሆነው ብቅ አሉ፡፡

ስለዚህም በሰዎችና-ሰዎች መካከል ያለው ግንኙነት ወደ ሰዎችና-ትርክት ሰንሰለት አደገ፡፡ ወይንም (ሰው – ትርክት – ሰው)

ትርክቱ ለአደን የረዳቸው፣ወይም ከበሽታና መቅሰፍት የጠበቃቸው አምላክ/አማልክትን ማምለክን እየጨመረ ሄደ፡፡

በይነ-ነቢባዊ አካላት (inter-subjective entities) ወይም የተወሳሰቡ ስሜታዊ አካላት

የተወሳሰቡ ስሜታዊ አካላትን ለማስረዳት ዩቫል ሀራሪ የሄደበት መንገድ ነገሮቹን በደንብ እንድረዳቸው ይጠቅመናል፡፡

እውነታ ሶስት አይነት ነው ይለናል ሀራሪ፡፡

የመጀመርያው ተጨባጭ እውነታ ነው (objective reality) ፡፡እነዚህ በእውን ያሉ ነገሮች ናቸው ለምሳሌ ድንጋይ፣ ወንዝ፣ ተራራ፡፡እኛ አሰብናቸውም አላሰብናቸውም አሉ -ይኖራሉ፡፡

ሁለተኛው ሕሊናዊ እውነታ (subjective reality) ነው፡፡ ስቃይ፣ደስታ፣ፍቅርን እንውሰድ፡፡ እነዚህ ጭንቅላታችን/ስሜታችን ውስጥ ያሉ እንጂ በተጨባጭ ያሉ ነገሮች አይደሉም፡፡ ካላሰብናቸው/ካልተሰሙን የሉም፡፡

ስሜቶች ደግሞ ቀስ በቀስ የተወሳሰቡ ስሜታዊ አካላትን ፈጠሩ፡፡

ሶስተኛ በይነ-ነቢባዊ አካላት (inter-subjective entities) ናቸው፡፡ እነዚህ ደግሞ የተወሳሰቡ ስሜታዊ አካላት ሆነው ግን  በአንድ ጊዜ በብዙ ሰው ጭንቅላት ውስጥ የሚገኙ፣ በሰዎች መካከል ያሉ ግንኙነት ክፋዮች ናቸው፡፡ ለምሳሌ ሐይማኖት፣ ሕግ፣ እና ገንዘብን ብንወስድ በተጨባጭ ምድር ላይ ያሉ እውነታዎች አይደሉም፡፡

እንደ ፍቅር እና ጥላቻ በአንድ ሰው ውስጥ የሚፈጠሩ ስሜቶች ሆነው ስለሌላ ሰው ወይም ነገር የሚሰሙን ስሜቶች ናቸው፡፡ ካላሰብናቸው አይኖሩም፡፡ በይነ ነቢባዊ አካላት ግን የብዙ ሰዎች ግንኙነት የፈጠራቸው አካላት ስለሆኑ አሰብናቸው አላሰብናቸው አሉ ይኖራሉም፡፡ አንድ ግለሰብ ስለ ሀገሩ ህግ ምንም ላያውቅ፣ምንም ላይሰማው ይችላል፡፡ ግን አንድ ጥፋት ቢፈጽም ለምሳሌ ሰው ቢገድል፣ ሰው መግደል ህገወጥ እንደሆነና ከባድ ቅጣት እንደሚያስከትል አሰበም አላሰበም ህጉን ከመኖር እሱንም ከመቀጣት አያድነውም፡፡

የተወሳሰቡ ስሜታዊ አካላት የሚፈጠሩት በመረጃ ልውውጥ ምክንያት ነው፡፡ በአንድ እንጀራ ውስጥ ያለውን የብረት ማእድን ይዘት በኛ አእምሮ ወይም እምነት ላይ አይወሰንም፡፡ ነገር ግን የእንጀራው ገንዘባዊ ተመን በሰዎች ግምትና እምነት ላይ ጥገኛ ነው፡፡ ነገር ግን በአንድ ሰው ፍላጎትና ግምት ላይ ብቻ ጥገኛ ሳይሆን ገዢ እና ሻጮች በሚያደርጉት የመረጃ ልውውጥ (መግባባት እና ስምምነት) አማካኝት የሚወሰን ነው፡፡ ገዢና ሻጭ ካላመኑበት የእንጀራው ዋጋ አይጸናም፡፡

በሰው ልጅ ግንኙነት ውስጥ ትርክቶች (የመረጃ አይነት ነው) ሰው አለምን እንዲገዛ ኃይል ቢሆኑትም ግን እንደ ገራገሮች እይታ (Naïve viez) ሁልግዜም ጥልቀት ያላቸው ጥበቦች ግን አይሆኑም፡፡

የገራገሮች እይታ መረጃ ወደ እውነት ሲወስደን እውነት ደሞ ሰዎችን ኃይልና ዕውቀትን/ጥበብን ያጎናጽፋቸዋል ብሎ ያምናል፡፡

እውቀት ያላቸው ሁሉ ኃይል የላቸውም፣ ኃይልን የተጎናጸፉ ሁሉም ጠቢቦች አይደሉም፡፡ ሁለቱ የሚገጥሙት በጣም አልፎ አልፎ ነው፡፡

ለምሳሌ ፊዚክስን ጠንቅቆ የሚያውቀው ሮበርት ኦፐንሄይመር የመጀመሪያውን የአውቶሚክ ቦምብ ሰራ(አሰራ)፡፡እውቀቱ አለው፡፡ ቦምቡ የትና መቼ ጥቅም ላይ እንደሚውል የወሰነው ግን ፕሬዚዳንት ሩዝቤልት ነበር፡፡ መጀመርያውኑም ኦፐንሄይመር የሩዝቬልት ተቀጣሪ ሆኖ በተሰጠው ትዕዛዝ መሰረት ነው ቦንቡን የሰራው፡፡

በታሪክ ብዙ ግዜ የሚሆነው ይህ ነው፣ ኃይል ያለው እውቀት ያለውን ያዛል፡፡

ግን ለምን ይህ ይሆናል?

ምክንያቱም ኃይል የሚመነጨው እውነትን ከማወቅ ነው፡፡ ቢሆንም ግን ያ በከፊል እውነታ ነው፡፡ ሌላው አስፈላጊ የኃይል ምንጭ ሰላምና መረጋጋትን (social order) በብዙ ሰዎች መካከል የመፍጠር ክህሎት ነው፡፡

በይነ ነቢባዊ አካላት እንግዲህ የተወሳሰቡ ስሜታዊ አካላት ናቸው፡፡ ለምሳሌ ሕግ፣ ሐይማኖት፣ ልምድ እና የመሳሰሉት፡፡ የበለጠ ወደ ምድር እናውርዳቸው ካልን – የፍትሀ ብሔር ሕግ፣ ክርስቲያንነት፣ እስላምነት፣ የጋብቻ ግርግር፣ የቀብር ስነስርዐት…

እንግዲህ ነገሩ እንዴት ነው፣ ኃይል እውነትም (ማለት እውቀት) ስነስርዐትንም ትፈልጋለች፡፡ ሁለቱ ካልገጠሙ ኃይል አይኖርም፣ ወይም አጥፊ ኃይል ነው ሊኖር የሚችለው፡፡

ምንም እንኳ ኃይል በእውነትም በስነስርዐትም የሚገኝና የሚጠበቅ ነገር ቢሆንም፣ ብዙውን ግዜ ሁሉን አሳማኝ ርእዮት አስፍነው እና ማህበረሰባዊ ስርዐት መፍጠር የሚችሉት ናቸው በእውቀት ለተካኑት፣ ስለዚህም ብዙ ነገር መፍጠር ለሚችሉት መመሪያ የሚሰጡት፡፡ ለዚህም ነበር ሮበርት ኦፐንሄየመር ለሩዝቬልት የሚታዘዘው፡፡

ወደቀደመው ምሳሌያችን ብንመለስ መሪዎች የሚያውቁት ግን ምሁራን/ሳይንቲስቶች የማይረዱት ምንድነው፣ ስለ ብዙ ነገሮች (ኬሚስትሪ፣ ፊዚክስ፣ ጂዖግራፊ) እውነትን (እውቀት) ማወቅ ማሕበረሰባዊ ሰላምና መረጋጋትን በብዙ ሚሊዮን ሰዎች መካከል ለማምጣት በቂ ነገር እንዳይደለ ነው፡፡

ቀዳማዊ ኃይለስላሴ ከሰዐሊው አፈወርቅ ተክሌ ጋር ብዙ ጊዜ ይጨቃጨቁበት የነበረ አንድ ጉዳይ ነበር፡፡ ልባርጉ እንግዲህ ያኔ በነበረው ስርአት አንድ የታወቀ ሰው የንጉሠ ነገሠቱን ግብር አክብሮ መጋበዝ አለበት፡፡ አፈወርቅ ተክሌ ግን ከጊዜ በኃላ ግብር መቅረት አመጣ፡፡ ተጠራና ንጉሠ ነገሥቱ ጋር ቀረበ-

‘‘ለምንድነው አሁን አሁን ግብር ላይ የማናይህ?’’

‘‘ጃንሆይ እግዜር ያሳይዎ፣ክርስቶስ ያመልክትዎ አጋፋሪዎቹ እኔን መጨረሻው ረድፍ አካባቢ ከተርታው ሰው ጋር ያስቀምጡና በእውቀት ከኔ በጣም ያነሱትን ደሞ ፊት ወንበር ስለሚሰጡ ነገሩ ትክክል ስላልመሰለኝ ነው’’

ይላቸዋል፣ ፈገግ ብለው

‘’በፊትም ያልንህ ይኸንኑ ነበርኮ! አንድ ሰው በአንድ እጁ ብዕር በሌላው ሰይፍ ከሌለው በብዕሩ ብቻ ሰይፍ ከጨበጠው እኩል አይሆንም፡፡ አንተ ሚኒስቴር ደ ኤታውንም ዲሬክተርነቱንም አልፈልግም፣ እየሳልኩ ነው መኖር የምፈልገው አልክ፡፡ አሁንም ያ ቢቀር በፊት እንዳልንህ ሹመቱን እንሰጥህና የሚገባህ ቦታ ያስቀምጡሀል’’

ጃንሆይ እንግዲህ ሹመት እንሰጥሀለን ሲሉ ፊታውራሪ ወይም ደጃዝማች ማለታቸው ነው፡ ሰዐሊው አፈወርቅ ደሞ ይህን መጠሪያ አልፈለገውምና እጅ ነስቶ ሹመቱን ሳይቀበል ወጣ፡፡

ወደ በኃላ በእሑድ ጠዋት ፕሮግራም ላይ አለ ሹመት ግን እኩዮቼ ናቸው ከሚላቸው ጋር በሁሉም ፕሮቶኮል ቦታዎች እንዲቀመጥ በተለይ አዘውለት እንደነበር ሲናገር ሰምቻለሁ፡፡

ወደ ቀደመው ነገራችን እንመለስና

የማሕበረሰባችንን መረብ አስተሳስረው ያያዙት ልብወለድ ትርክቶች፣ በተለይም ስለ ፈጣሪ፣ገንዘብ፣ አገር እና መሰል ነገሮች የተወሳሰቡ ስሜቶች አካላት (Intersubjective entities) ናቸው፡፡

አንድ ሳይንቲስት የሳይንስ አካዳሚ አባላትን ሰብስቦ አዲስ ስላወጣው የፊዚክስ ግኝት በተሳለ ቋንቋ ቢያስረዳቸው ለሰዐታት አፋቸውን ከፍተው ያዳምጡታል፡፡ ያንኑ ዲስኩር በመገናኛ ብዙኀን ቢለቀውሳ? አድማጭ ተመልካቹ ጣቢያውን ቀይሮ ዘፈን ይኮመኩማል እንጂ ራሱን በተወሳሰበ ቀመር አይበጠብጥም፡፡ ኑሮ የሚያናጥበው ይበቃዋል፡፡

ሕዝብን በማስተባበር ረገድ የፈጠራ ታሪኮች ከዕውነት የሚበልጡበት ሁለት ምክንያት አላቸው፣ አንደኛ የፈጠራ ታሪኮች በምንፈልገው ልክ አቅለን ልናቀርባቸው እንችላለን – እውነት/እውቀት ግን ውስብስብ ነው፡፡ ሁለተኛ እውነት/እውቀት ብዙውን ግዜ ያማል አይመችም፡፡ ፈጠራ ግን አዝናኝ ነው በውሸትም ቢሆን፡፡

ካፒቴን ስምረት ብርሀኔ በሸገር የጨዋታ እንግዳ ሆነው የተናገሩት አንድ ቁም ነገር አለ፡፡ እንግዲህ እሳቸው የአፍሪካ አየር መንገዶች ማሕበር መሪ ሆነው ሳለ አንዳንድ የአፍሪካ ሀገር አየር መንገድ ኃላፊዎች ድርጅታቸው እንደ ኢትዮጵያ አየር መንገድ ለምን ውጤታማ እንዳልሆነ እንዲያስረዷቸውና ምክር እንዲሰጧቸው ያስቸግሯቸው ነበር፡፡ እሳቸው ግን ለሚጠይቃቸው ሁሉ

‘’ይቅርብህ ወንድሜ፣ ለጠየቅኸኝ ጥያቄ እውነቱን ከመለስኩልህ ትጣላኛለህ’’ እያሉ በጸባይ ይሸኙ ነበር፡፡ አንደኛው ግን አይ እውነቱን ነግረውኝ እመሸበት ልደር ብሎ አለቅ ይላቸዋል፡፡ ቃል ለቃል ባይሆንም የሚከተለውን ይነግሩታል

‘‘አየህ ችግሩ ያለው በከፊል እናንተ ስራ አስኪያጆቹ ጋ ነው፡፡ ገና እንደተሾማችሁ የሉፍታንዛ ስራ አስኪያጅ ደመወዝን ትጠይቁና የኛም በዛ ልክ ካልሆነ ትላላችሁ፡፡ ብትመከሩ እሺ አትሉም፣ እሱ ነጭ እኔ ጥቁር ስለሆንኩ ነው ትላላችሁ፡፡ ደሞ ያም በበቃ ሶስት አራት ረዳቶችን በወፍራም ደመወዝ ትቀጥራላችሁ፡፡ ለምሳሌ የአንደኛው ረዳት ስራ ለጉብኝት በሄዳችሁበት አገር የአልቤርጓችሁ አልጋ ላይ ሁለቴ ከነጠረ በኃላ ምቹ መሆኑን የሚያረጋግጥ ነው፡፡ ታድያ አየር መንገዳችሁ ይህን ሁሉ ወጪ ሸፍኖ እንዴት አትራፊ ይሆናል?’’ ብለው መለሱለት፡፡

ሰውየው ተናዶ ደህና ሁኑም ሳይላቸው የቢሯቸውን በር በርግዶ ወጣ፡፡

እና እውነት/እውቀት ይከብዳል

እስካሁንም እኮ ብዙዎቻችን የአነስታይንን የ ኢ ኤም ሲ ስኩየርን ቀመር አልተረዳነውም፡፡

በርግጥ አንዳንድ በጣም ጥቂት የሆኑ የእውቀትና የእውነት ሰዎች በብዙሀኑ ሊደነቁና ሊወደዱ በቅተዋል፡፡

አንድ ጊዜ በለንደን ለገሐር ይመስለኛል ጋዜጠኞች ቻርሊ ቻፕሊን እና አልበርት አነስታይንን አንድ ላይ ያገኟቸዋል፡፡

አንስታይን ቻርልስ ቻፕሊንን ‘’ስላንተ በጣም የሚገርመኝ ምን መሰለህ? ያንተ ጥበብ ሁለንተናዊነቱ (universality) ነው፡፡ ምንም ቃል አትናገርም፣ ከእንቅስቃሴህ ብቻ ሰው ሁሉ የይረዳሀል’’ አለው፡፡ ቻርሊ ቻፕሊንም ሲመልስ

‘’ያንተ ግን የበለጠ ይገርማል፡፡ ምክንያቱም፣ አለም ያደንቅሀል፣ የሚያደንቅህ ግን ሳይረዳህ ነው’’

ለማንኛውም አነስታይን ልዩ ሳይንቲስት ስለሆነ ነው ሰው የወደደው፡፡ብዙ፣በጣም ብዙ ግዜ ግን ሕዝብ ሳይንቲስቶች ስለመፈጠራቸውም አያስታውስም፡፡ ለዚህ እኮ ነው ቲቪያችንና ሬድዮናችንን የሚያጨናንቁት ያወቁ ሳይሆኑ የታወቁ ሰዎች የሆኑት፡፡

እንዲህም ስላልን ግን ሁሉም ፖለቲከኞች ውሸታም ናቸው ሁሉም ብሔራዊ ታሪኮች ሐሰት ናቸው ማለታችን አይደለም፡፡ ልብ በሉ! ብዙውን ግዜ ምርጫው እንዲያው በቀላሉ እውነትን መናገርና መዋሸት እንዳይመስለን፡፡

ለምሳሌ የንግሥተ ሳባንና የሰለሞንን ታሪክ እንውሰድ፡፡ በጥንት ጊዜ ንገሥታቱ ተቀባይነትን ለማግኘት ስልጣነ-ቡራኬያቸው ምድራዊ ሳይሆን ሰማያዊ መሆኑን ማሳመን ነበረባቸው፡፡ በዚህ ረገድ የኛ ሰለሞን ዘሮች ብቻ አይደሉም ይህን የሚያደርጉት፣ የዮርዳኖሱ፣የሞሮኮውና የሳዑዲ ነገስታት ሁሉም የነቢዩ መሐመድ የልጅ ልጆች እንደሆኑ ነው ሲተርኩ የኖሩት፡፡

ለዚያን ግዜው ማሕበረሰብ ሰላምና መረጋጋት ረድቶ ይሆናል ብለን እንለፈው፡፡

በዚህ ረገድ የፈጠራ ትርክቱ ውሸት የሚሆነው ትርክቱ እውነት ነው ብለን ከተከራከርን ነው፡፡ ይህ ሳይሆን ትርክቱ የሀገርን በሀገርነት ለማቆየት አስፈላጊ የነበረ የተወሳሰበ ስሜት (ኢንተር ሰብጀክቲቭ ሪያሊቲ) ነው ማለቱ የተሻለ ነው፡፡

በነገራችን ላይ አሁን አየተነገሩ ያሉ ፈጣጣ ውሸቶችን እውነት ናቸው ብለው ሊያሳምኑን የሚሞክሩ ፖለቲከኞች፣ የሳባ-ሰለሞንን ትርክት ውሸትነት ለማስረዳት ሲጥሩ ማየት ፈገግ አያሰኝም?

እዚህ ጋ አንድ ነጥብ አስቀምጠን እንለፍ፣ ማህበረሰባዊ ስርአት ማለት ከፍትህ እና ርትዕ ጋር እንዳናምታታው፡፡ ለምሳሌ የአሜሪካው ሕገመንግስት በሰው እንደተጻፈ እና ሊሻሻል የሚችልበትን አግባብ ያስቀምጣል፡፡ ይህ እንግዲህ በፍትህ እና ርትዕ ረገድ ያለበትን ክፍተት አምኖ ለማሻሻል እድል ያስቀመጠ ነው ማለት ነው፡፡

ሁሉም ሰው የዘረጋው የመረጃ መረብ ሁለት ነገሮችን በአንዴ ማሳካት አለበት እውነቱን ማስቀመጥ እና ስርአትን ማንበር!!

ከዚህ በተያያዘ ከመረጃ መረብ ጋር ያለው ችግር ምንድነው? በራሱ መረቡ እውነትን ሊሻና ለማግኘት የሚያበረታታ ሊሆን ይችላል፡፡ ግን ይህን የሚያደርገው በተወሰኑ መስኮች ብቻ ነው፡፡ የእነዚህ መስክ ጠበብቶች ተግባርም የማህበረሰቡን ስርአት ሳይነካ ወይም የፖለቲካ ፍልስፍናውን ጠብቆ ግን ኃይል ማሳደግ ይሆናል፡፡

በማርክሲስት ራሺያ፣ በናዚ ጀርመን፣ እና በሺአይት ኢራን ያሉ ሳይንቲስቶች ሁሉ ይህን ሲያደርጉ ነበር አሁንም ያደርጋሉ

ለማንኛውም የመጀመርያው የመገናኛ ቴክኖሎጂ፣ ማለት አይቲ ትርክት ነበር፡፡ የሚዘዋወርበት ዘዴው ደሞ ከአፍ- ወደ አፍ ነው፡፡

ሁለተኛው ትልቁ የመረጃ ቴክኖሎጂ አይነት ሰነድ ነው

ምዕራፍ ሶስት

ሰነዶች የሚናከስ የወረቀት ነብር (paper tiger?)

ጫካ ውስጥ የፈለጉትን እንደሚያገኙት እንደ አዳኞችና ፍራፍሬ ለቃሚዎች ሳይሆን የመዝገብ ቤት ሰራተኞች ዶሴዎችን በስነስርዐት የሚመሩበት ስርዐት ያስፈልጋቸዋል፡፡ ይህም ስርዐት ቢሮክራሲ ይባላል፡፡ ይሁንና ታድያ ቢሮክራሲም እንደ አፈታሪክ (ትርክት) ሁሉ እውነትን ስነስርዐት ለማንበር ሲል ይገለዋል፡፡

በዚህ የመረጃ ቴክኖሎጂ ዘመን ሰነዶች ከፍተኛ ዋጋ ያላቸው መረጃዎች ሆነው ተገኙ፡፡ ለመሆኑ መሰነድ ለምን አስፈለገ? በአፈታሪክ ላይ ተመስርቶ የነበረው የመረጃ ስርዐት ራሱን ለማየት እና ለማስቀጠል ያለፉትን አፈታሪኮች ከአፍ ወደ አፍ እየተቀባበለ ያስተላልፋቸው ነበር፡፡ በዚህ ሂደት አፈታሪኮቹ ቀስ በቀስ በትንሽ በትንሹ እየተለዋወጡና አንዳንዴም እየተሻሻሉ፣ ብሎም እየተቀያረየሩ ቀጠሉ፡፡

ይህ ማለት ምንድነው? አንዳንድ መረጃዎችን በቃል ማስተላለፍ እያዳገተ መጣ፡፡ ለምሳሌ በግብጽ ፋሮዎች ዘመን ቁጥሮች አስፈላጊ እየሆኑ መጡ፡፡ የአባይ ውኃ ደለል ይዞት የመጣው አፈርን እኩል ለገበሬዎች ለማከፋፈል ሂሳብ መስራት አስፈለገ፡፡ ያን በቃል አስታውሶ በትርክት ብቻ ማከናወን አይቻልም፡፡ ቁጥሮችን በስዕልም ሆነ በምስል ማስቀመጥ ግዴታ ሆነ፡፡

ወደ በኃላ የመጣው ማሕበረሰብ ግን እያደገና እየሰፋ የሚተዳደርበት ስርዐት ስርዐቱን የሚያስፈጽሙ አካላትን መገንባት አስፈለገው፡፡ እነዚህ አካላት ማሕበረሰቡን በስርዐት ለመምራት ሰዎችን መቅጠር፣ የተቀጠሩት ሰዎች የሚሰሩበት ቢሮ፣ ደመወዛቸውን ለመክፈል ደሞ ከማሕበረሰቡ ገንዘብ በቀረጥ መልክ መሰብሰብ አስፈለገ፡፡

እነዚህ ስራዎች በትውስታ ብቻ ሊከናውኑ አይችሉም፡፡ ነዋሪው መመዝብ፣ ለከፈለው ቀረጥም ደረሰኝ አስፈለገው፡፡ የከፈለውንና ያልከፈለውን ለመለየት፣ የተከፈለውን መጠን አስልቶ ለንጉሡ ለማስረገብ በጽሁፍ የተቀነባበሩ ዶሴና ሰነዶች እዚህም እዚያም ብቅ ብቅ ማለት ጀመሩ፡፡

መጀመርያ በጭቃ ከተሰሩ ሰሌዳዎች ላይ ነዋሪው ያለው ፍየል በቁጥር ይቀመጣል፣ ከዚያ ላይ አስራቱ ተሰልቶ እንዲያስረክብ ይደረጋል፡፡ የርክክብ ሰነድ እና ዶሴ ስራ ይጀምራሉ፡፡

በቁሙ ቢሮክራሲ መጻፊያ ጠረቤዛ ከሚለው ቃል የተወለደ ነው፡፡የንጉሥ ተቀጣሪው በቢሮ ወንበሩ ላይ ቁጭ ብሎ በጠረቤዛው ላይ  ዶሴዎቹን በጽሁፍ አዘጋጅቶ ይሰንዳል፡፡ በተፈለጉ ጊዜ ቶሎ እንዲገኙ የተለያዩ ሰነዶች በተለያዩት የጠረቤዛው መሳቢያዎች ያስቀምጣል፡፡ የየሰዉ ንብረት (ከብት፣እሕል፣ማር…ወዘተረፈ)ዝርዝር በአንድ መሳቢያ፣የተከፈለ ቀረጥ ደረሰኝ በሌላ፣ ያልከፈለ ሰው የእዳ ሰነድ በሶስተኛው መሳቢያ…እያለ ይቀጥላል፡፡

‘ከፋፍለህ ግዛ  ሀ ተብሎ ተጀመረ’ – ቢሮክራሲ!!

ሰዉም ውል መዋዋል፣ ብድር መበዳደር ጀመረ፡፡ የውል ሰነድ፣ የእዳ ማረጋገጫ ሰነድ…

የከፈልክበት ደረሰኝ ወይም ያበደርክበት ውል ከሌለህ ክፍያህም አይጸና ያበደርከውም አይመለስልህም፡፡ እግዚአግሔርን የፈራ አምኖ ካልረዳህ፡፡

ቀረጥ ለመጣልም ሆነ ለመሰብሰብ የቃላት ሰነድ ብቻውን የተሟላ ስለማይሆን ቁጥሮችም ተፈልስመው ከቃላት ጋር ተሰናስለው አንድን ሰነድ የተሟላ መረጃ እንዲሆን አረጉት፡፡ አሁን ቢሮክራቶች ማንበብና መጻፍ ብቻ የተካኑ ሳይሆኑ ሒሳብ አዋቂዎችም ሆነ፡፡ ስለዚህ የሀይማኖት/ፍልስፍና እውቀት ላይ የሒሳብ ጥበብም በስራ ላይ መዋል ጀመረ፡፡ አልጀብራና ጂዖሜትሪ !

በዚህ አይነት ሰነዶች የእውነታ ነጸብራቅ ወኪል ብቻ ሳይሆኑ ራሳቸውም እውነታ ሆኑና አረፉት፣ መረጃውን የሚይዙት ደሞ ኃይለኞች እየሆኑ መጡ፡፡ ምክንያቱም ብዙ ሰው የሌላቸው ግን እነሱ ያላቸው ነገር አለና! ይህም ሰነድ ነው፡፡ መረጃ

አንተ የበታች ሹም የኔ ሀሳብ ሰጪ

ዶሴዬን መርምረው አይሁን ተቀማጭ፡፡

እንዲታይ ነው እንጂ ወደ በላይ ቀርቦ

መች እንዲኖር ነበር መዝገብ ቤት አጣቦ

የአባይ በለጠ ቆየት ያለ ዘፈን፡፡ ምድር ጦር ሰራዊት ኦርኬስትራ

ከሰው-ወደ-ሰው የነበረው የመረጃ ግንኙነት ፍሰት ከሰው-ወደ-ሰነድ ሆነ

ሰዎች ባለስልጣንና ተራሰው ሆነው ተከፋፈሉ፡፡ቀለም ቀመሶቹ ቢሮከራቶች የማዕከላዊ አገዛዙን ኃይል አጠናከሩት፡፡ እያንዳንዱ ሰው ቢሮክራሲው እንዴት እንደሚሰራ እውቀት ስለሌለው ማዕከላዊ መንግስቱን መሸወድም ማምለጥም የማይችል ሆነ፡፡

በሌላ በኩል ግን መልክ ያለው ስርዐት ሰፈነ፡፡ ሰነድ የጊዜው የመረጃ ቴክኖሎጂ ሆኖ ነገሠ፡፡

እስካሁንም!!

የጽሁፍ መፈጠርና መሻሻል አፈታሪኮቹ እና ትርክቶቹ በጽሁፍ መልክ እንዲቀርቡ በር ከፈተ፡፡ መጽሐፍ ቅዱስ፣ ቅዱስ ቁርአን፤ የሕንዶቹ ቬዳ የየሕብረተሰቡ ማሕበራዊ ሕይወት ውስጥ ቁልፍ ሚና መጫወት ጀመሩ

ምዕራፍ አራት

ሕጸጾች: የእምነቶችና የእምነት መጻሕፍት ምሉዕ-በኩለሄነት

የሰው-ሰነድ ግንኙነት የመረጃ ቴክኖሎጂ ቢሮክራሲያዊ ስርአትን እና ሒሳብን ብቻ ሳይሆን የቀድሞ አፈታሪክ እና ትርክቶችን በአንድ በመሰነድ ለየ ማሕበረሰቡ ለአለማዊው ሕግ ጋር ወይም  ጎን ለጎን መሪ ሕግጋት ሆኑ፡፡

በየመጻሕፍቱ የተጠረዙት ሐይማኖቶች በሰው ከሰው አዕምሮ የፈለቁ በሰው እጅ የተጻፉ ሳይሆኑ መለኮታዊ ደራሲ አግኝተው የማይሻሩ የማይለወጡ ምሉዕ በኩለሄ ድንጋጌዎች ተደረጉ፡፡

እነዚህ መጻሕፍት ግን ራሳቸውን ስለማይተረጉሙ ቱርጁማኖች ተደረጉላቸው፡፡ ቀሳውስት፣ሼካዎችና ብራሀማዎች ከቢሮክራቶቹ እኩል እንዲያውም ቀደም ሲል ከነሱም የበለጠ ስልጣን ተጎናጸፉ፡፡

የሀይማኖት ጠቢባኑ ማለት ቴዎክራቶች ብዙ ጊዜ ከአለማዊው ዘውድ እኩል አንዳንዴም የበላይ እየሆኑ የሰው-ሰነድ መገናኛ ቴክኖሎጂውን ይመሩት ነበር፡፡

ቴዎክራቱን የተገዳደረ፣ለመገዳደር ያሰበ፣ በመገዳደር የተጠረጠረ አይቀጡ ቅጣት የሚቀበልበት አሰራር ተስፋፋ፡፡ ጠንቋዮችን የማስወገድ ዘመቻዎች፤ የአይሁድ ዕምነት ተከታዮች ላይ ያነጣጠረው የስፓኒሽ ኢንኩዚሽንን ያስታውሷል፡፡

ሆኖም ከዕውነት ይልቅ እምነት ያመዘነበት አሰራር ዘለአለማዊ መሆን አልቻለም፡፡ ከዚህም ከዚያም ተገዳዳሪዎች ተነሱበት፡፡

በሰው-ሰነድ የመገናኛ ቴክኖሎጂ ትልቁ እመርታ የደረገው ዮሐንስ ጉተንበርግ በ 1440 የሕትመት መኪና (Type Writer) ሲፈለሰፍ ነው፡፡

ከዛ በፊት ሰነዶች በሰው ሲጻፉና ሲገለባበጡ እንደ ከራኒው እውቀትና ትጋት ሊቀነሱ፣ሊዛቡ ከመቻላቸውም በላይ አንድን መጽሐፍ በብዙ ግልባጭ ለመጻፍ የሚወስደው ጊዜ እና የቅጂው ብዛት ውሱን ነበር፡፡ የህትመት መኪናው በዚህ ረገድ ያመጣው መሻሻል አብዮታዊ ነበር ቢባል ማጋነን አይሆንም፡፡

ይህም ለእውቀት መስፋፋት ትልቅ አስተዋጽዖ አድርጓል፡፡

የጽህፈት መኪና ((Type Writer)

እኔ እማውቀው አለማወቄን ነው (ሶቅራጥስ)

ጊዜው እየተሻሻለ ሲሄድ እና እውቀት እየስፋፋ ሲመጣ ቴዎክራቶቹ የሚመሯቸው የሀይማኖት ተቋማትና የማይሻሩ የማይለወጡ ሕግጋቶቻቸው ከዘመኑ ጋር ለመጣጣም አልቻሉም፡፡

አዲስ እያበበ የመጣው እውቀት ሳይንስ ነው

ልክ እንደ ቤተእምነቶች የሳይንስ አላማም እውነትን ማግኘት ነው፡፡ የበፊተኛው እውነትን በእምነት እንዳገኘ የሚያምንና ያም የማይለወጥ እና የማይሻሻል እውነት እንደሆነ ይደነግጋል፡፡

ሳይንስ በበኩሉ እውነትን ከእምነት ብቻ ሳይሆን በይበልጥም በእውቀት በኩል ለማግኘት ይጥራል፡፡ የአንድን ነገር እውነታ ሙሉ በሙሉ ይሄ ነው ብሎ ለመደምደም ያለው እውቀት ውሱን መሆኑን አምኖ የተደረሰበት እውነት በፈቲነ-ግብር (Experiment) እየተረጋገጠ፣ እየተሻሻለ ሊለወጥ እንደሚችል እድል ያስቀምጣል፡፡

ስለዚህ ሳይንስ አንድን ነገር ሲመረምር ያን ነገር ሙሉ በሙሉ ካለማወቅ ይጀምራል፡፡ ላቲን ይህንን ኢግኖራሲየም ይለዋል፡፡ ሶቅራጥስም ‘’እኔ የማውቀው አለማወቄን ነው’’ እንዲል

እስቲ ለነገሩ ወይም ለችግሩ የተለያየ መፍትሔ እና መላምት እናስቀምጥለት፣ መላምቶቹን በፈቲነ ግብር ፈትሸን እውነቱ ላይ እንድረስ፡፡ የተደረሰበት እውነት በየጊዜው የሚፈተሸ፣ የሚሻሻልና ካስፈለገም የሚተካ ነው፡፡ በሚል ጽኑ መሰረት ላይ ነው የቆመው ሳይንስ፡፡

የአንድን እውቀት እውነታነት ለማረጋገጥ ተቆጣጣሪ ወይም አስተካካይ ተቋማት ያስፈልጋሉ፡፡ እነዚህ ተቋማት ጥናትና ምርምር አድርገው ውሳኔያቸው እውነት እና እውነትን ብቻ መሰረት ያደረገ ነው፡፡ በዚህ አይነት የተደረሰበት እውነት ወይም እውቀት ቢሆን በየጊዜው የሚፈተሸበት ስልት/ሕግ ይቀመጥለታል፡፡ ስለዚህም ገና ከመወለዱ የመሻሻልና የመለወጥ አንቀጽ ተቀምጦለት ነው የሚደነገገው፡፡

በሌላ አነጋገር የሳይንሳዊ አብዮት የተመሰረተው ለአለማወቅ (Ignorance) እውቅና በመስጠት ነው፡፡

የግለእርምት ዘዴ  The limits of self-correction

ሁሉም ነገር ማለት ሰው፣ማህበረሰብ፣ ተፈጥሮም ጭምር የማያቋርጥ የራስ በራስ የማሻሻያ ዘዴ አለው፡፡ ይህ ዘዴ መስራት ሲያቆም ያ አካል (entity) ይሞታል፡፡

ሰውነታችን የሞቱና የደከሙ ሴሎችን አስወግዶ በአዲስ ይተካል፣ አዳዲሶቹ ሴሎች በተራቸው ሲደክሙና ሲያረጁ በሌላ ይተካሉ፡፡ ይህ ሂደት በሕይወታችን ሁሉ ሰውነታችን በራሱ የሚያካሂደው ክስተት ነው፡፡ ይህን ማካሄድ አቅቶት አሮጌ ሴሎችን በአዲስ ካልተካ እንሞታለን፡፡ ከዚያ የሚከተለው ስርዐተ-ቀብር ነው፡፡

የአሜሪካ ሕገመንግስት ከሁለት መቶ አመት በፊት ሲደነገግ ካስቀመጣቸው አንቀጾች አንዱ ሕገ-መንግስቱ በምን መንገድ እንደሚሻሻል ነው፡፡ በዚህም መሰረት እስካሁን ሀያ ሰባት ጊዜ ተሻሽሏል፡፡ ባርነት እንዲቀር የተደረገው፣ ጥቁሮችና ሴቶች የመምረጥ መብት ያገኙት በነዚህ መሻሻሎች ነው፡፡

በሳይንስ አለም አንድ የተከበረ ግኝት ወይንም እውነታ በግለ-እርምት ዘዴ በሌላ ሲተካ ኹነቱ (event) ትልቅ በዐል ሆኖ ይከበራል፡፡ ለሁለት መቶ አምሳ አመት ጸንቶ የነበረው የአይዛክ ኒውተን ሎው ኦፍ ሞሽን በአልበርት አነስታይን ስፔሻል እና ጄኔራል ሪላቲቪቲ ሲሻሻል ትልቅ ደስታ ነው የፈጠረው እንጂ ቅሬታን አላስተናገደም፡፡ የጄኔራል ሪላቲቪቲን ፈቲነ-ግብር አፍሪካ ድረስ በመሄድ በተግባር ያረጋገጠው የኒውተን አገር ሰው እንግሊዛዊ ነው፡፡

ለዚህ ነው ሳይንስ ለእውነት በጣም የቀረበው፡፡

 የግለእርምት ውሱንነት

ግለ-እርምትም ቢሆን ታድያ የራሱ ውስንነቶች አሉት፣ ምንም ነገር ምሉዕ-በኩለሄ አይደለምና!

ቀደም ሲል እንዳስቀመጥነው በመገናኛ ቴክኖሎጂ አሰራር የምንከተለው ቴክኖሎጂ ወደ እውነት የሚያደርሰን ብቻ ሳይሆን ማሕበረሰባዊ ስርዐትን የማያደፈርስ መሆን አለበት፡፡

ፖለቲከኖች ለስነስርአት ሲሉ እውነትን እንደሚጫኗት ሁሉ አንዳንዴ የምንጠቀምበት የመገናኛ ቴክኖሎጂ ለእውነት ሲል ማሕበራዊ ሰላምን ሊያደፈርስ እድል እንዳለው መገንዘብ ጠቢብነት ነው፡፡

የመገናኛ ቴክኖሎጂ ትልቅ ግብ ትልቅ የስነስርአት መዛባት ሳይደረስ የተገኘውን እውነት በስራ ላይ ማዋል ነው፡፡ በእውነትና በስነ-ስርአት መካከል ያለውን ሚዛን መጠበቅ ይኖርብናል፡፡

በ 1983 ግንቦት ላይ የጊዜው የሕንድ ጠቅላይ ሚኒስቴር ራጂብ ጋንዲ በአንዲት አጥፍቶ ጠፊ ይገደላሉ፡፡ አጥፍቶ ጠፊዋ የሲክ ዘውግ አባል ነች፡፡ ሲኮች የእምነት ነጻነታችን ተነካ ባሉበት ወቅት ሀይለኛ ረብሻ ይፈጥራሉ፡፡ ቀደም ሲል የሲኮች ምኩራብ በሂንዲዎች ሲቃጠል ኢንድራ ጋንዲ ምንም እርምጃ አልወሰደችም በዚህም የድርጊቱ ተባባሪ ናት ብለው ያመኑ ሲክ ዘቦቿ እሩምታ ጥይት አርከፍክፈው ገድለዋታል፡፡

ወዲያውኑ ብዙሀኑ የሂንዱ ማሕበረሰብ በንዴት ግሎ በየቦታው ያገኛቸውን ሲኮች ከመግደሉም በላይ የንግድ ተቋሞቻቸውንና ምኩራቦቻቸውንም አንድዶባቸዋል፡፡ ረብሻውና ግድያው በመከራ ነበር የቆመው፡፡

አሁን ታድያ የኢንድራ ጋንዲ ልጅ በተመሳሳይ በሲክ አጥፍቶ ጠፊ ሲገደል የሕንድ መንግስት የወሰደው የመጀመርያ እርምጃ ወዲያውኑ ግድያውን የፈጸመችው የሲሪላንካ አክራሪ ድርጅት አባል የሆነች ሴት መሆኗን አሳወቀ፡፡ ሁሉም የመገናኛ ብዙሐን ይህንን ተቀብለው አስተጋቡት፡፡

ነገሩ ውሸት ነው፣ ግን የብዙ ሺ ሲካውያን ሕይወት ተረፈ፡፡ አገሪቱም ምንም አይነት የጸጥታ ችግር ሳይገጥማት አለፈ፡

ለማንኛውም አስተያየት ካላችሁ itaye4755@gmail.com ላይ እንገኛለን

Yuval Noah Harari, Nexus: A brief History of Information Networks from Stone Age to AI: Penguin Random House UK, 2024

Add post to Blinklist Add post to Blogmarks Add post to del.icio.us Digg this! Add post to My Web 2.0 Add post to Newsvine Add post to Reddit Add post to Simpy Who's linking to this post?

ጸኃይ 28 Feb 3:12 AM (14 days ago)

ጸኃይ

በ 2007 ድሬደዋ እያለሁ ለገሀር ከመኮንን ቡና ቤት አካባቢ በረንዳ ላይ የማይጠፋ አንድ ወፈፍ የሚያደርገው ወጣት ነበር፡፡ መልከ መልካም እና መለሎ የሆነውን ይህን ወጣት የማስታውሰው በአንድ ምክንያት ነው፡፡ አንዳንድ ጊዜ ፊቱን ወደ ጸኃይ ቀና ያደርግና አይኑን በእጁ እንኳን ሳይሸፍን ትክ ብሎ ጸኃይቱን ያያል፡፡ ያውም እስከ ሶስት አራት ደቂቃ ድረስ፡፡ እንደምታውቁት የድሬ ጸኃይ ገና በጠዋቱ እንኳ ሀይለኛ ነች፡፡ ታድያ ይኼ ወጣት ምን አይነት ልዩ ኃይል ቢኖረው ነው ትኩር አድርጎ ጸኃይን ለማየት የቻለው?

ፈረንጅ አገር ቢሆን የሳይንስ እና ምርምር ተቋማቱ የዚህን ሰው አይኖች ልዩ ችሎታ ‘’አጃኢብ’’ እያሉ ባላሳለፉት፡፡

‘’ጸኃይ’’ የዚህ ወር የሳይንስ አምዳችን ትኩረት ነች፡፡ የኃይል እና የብርሀን ምንጭ፣ በአካባቢያችን ካሉት ዋና ዋና የፍጥረት አካላት ትልቋ፣ከጠቀሜታም አንጻር ጸኃይ ዋናዋ የተፈጥሮ አጋራችን ናት፡፡ መሬታችን ኃይሏን የምታገኘው ሙሉ በሙሉ ከጸኃይ ነው፡፡ ተክሎችና እጽዋት ለእድገታቸው ጸኃይ ወሳኙን ሚና ትጫወታለች ስለዚህ ነው አርሰን መብላት የምንችለው ፡፡ በዘመናችን ሳይንስ ጣራ ላይ በሚተከሉ ሰሀኖች አማካይነት የጸኃይ ኃይልን በመግራት ወደ ኤሌክትሪክ በመቀየር ለዘርፈ ብዙ አገልግሎት እያዋለ ነው፡፡ ጊዜን ማለትም ቀንና ሌሊትን እንዲሁም አመትን የምንቆጥረው አንዱም በጸኃይ ነው፡፡

ብቻ የጸኃይ ጠቀሜታ፣ ለምድራችንም ህልውና (በተለይም ለፍጥረታት) ወሳኝ አካል እንደመሆኗ ጸኃይን በደምብ ማወቅ ጠቃሚም አስፈላጊም ነው፡፡ እስቲ ጽሁፋችንን በቀላል ጥያቄ እንጀምር፣ ጸኃይ ምንድን ነች?

በዚህ መጣጥፍ የሰው ልጅ የጸኃይን ማንነት ለማወቅ ከጥንት እስካሁን ድረስ ያደረገውን ጥረት እንመለከታለን፡፡ ለዚህ ጽሁፍ ግብአት ብዙ ምንጮችን የተጠቀምን ቢሆነም፣ በዋናነት መነሻ ሀሳቡን እና አወቃቀሩን ያገኘው በ 1999 የቢቢሲ ቴሌቪዥን ካቀረበው ‘’The Planets’’ ከተሰኘው ዘጋቢ ፊልም  ነው፡፡ በተጨማሪም ከናሳ ያገኘናቸውንም መረጃዎች ተጠቅመናል፡፡

መቼም ይህን ታሪክ አንድ የህዋ ሳይንስ ባለሙያ ቢተርከው እንደምን ባማረ፡፡ለአሁኑ ባለን የምንችለውን እናቀርባለን፡፡ የመስኩ ባለሙያዎች የምትሉትን ለመስማት፣ የምታቀርቡትን ለማተም ዝግጁ ነን፡፡

ባጭሩም ከዚህ በታች የምንተርክላችሁ ታሪክ ሰው ስለ ጸኃይ ለማወቅ ያደረገውን ጥረት፣ የጸኃይ ሀይል ወሰኑ እስከምን እንደሆነና፣ በተጨማሪም ጸኃይ በአጽናፈ ሰማይ (ዩኒቨርስ) ውስጥ ያላትን ሚና መተንተን ይሆናል፡፡

ፕሮፌሰር ዲያጎ በቢቢሲ ዘጋቢ ፊልም ላይ እንዳለው፣ አያት ቅድመ አያቶቻችን ጸኃይን የሚመለከቷት እንደ አንድ ፀአዳ ፍጥረት ነበር፡፡ ምንም እንከን የሌለባት ዲስክ! ምንም እድፍ የሌለባት ፀአዳ (ፐርፌክት) ነገር፡፡ ሰማይ ፀአዳ ነው፣ ፀኃይ ደሞ በዚህ ፀአዳ ቀላይ ውስጥ ያለች የፀአዳ ፀአዳ፡፡ (BBC Documentary ; The Planets : 1999)

ደራሲና ጸኃፌ ተውኔት ከበደ ሚካዔል የቅኔ ውበት በተባለ መጽሀፋቸው ስለሙዚቃ ሲገጥሙ ከጸኃይ ፀአዳነት ጋር እያነጻጸሩ ነበር፣- ግጥሙ በደንብ ካስታወስኩት

         ፈልቀሽ የተገኘሽ ከሹበርት ራስ

         ከሾፐን ትካዜ ከያሬድ መንፈስ

         ከሞዛርት ቅላጼ ከቤቶቨን ናላ

         መዓዛ የሞላብሽ  የብስጭት ቃና

       ውቢቷ ድምጽ ሆይ ረቂቋ ሙዚቃ

       ንጽኅት እንደ ጸኃይ ውብ እንደ ጨረቃ

ስለዚህም የሰው ልጅ በፈጣሪ ማመን ሲጀምር ‘’ጸኃይ’’ የመጀመርያዋ በፈጣሪነት የተመለከች አካል ሳትሆን አትቀርም፡፡ ከታሪክ እንደምንረዳው ‘’የጸኃይ አምላክ’’ በብዙ ጥንታዊ ስልጣኔዎች ትልቅ ስፍራ የነበረው አምላክ ነበር፡፡ በግብጽ የጸኃይ አምላክ ‘’ራ’’፡፡ በጥንታዊ ግሪኮች ‘’ሂሊዮስ’’ እንዲሁ የተከበረ  ነበር፡፡ በሀገራችንም ፍትሐ ነገሥት እንደተረከው፣ ንግሥተ ሳባ ኢየሩሳሌም ንጉስ ሰለሞን ጋ ከርማ፣ ብሉይ ኪዳንን ተቀብላ ስትመለስ፣ ‘’እኔ ጸኃይን ሳይሆን፣ ጸኃይን የፈጠረውን አምላክ ነው የማምነው’’ ብላለች ይላል፡፡ ይህ ማለትም ከዚያ በፊት በሀገራችን ጸኃይ ትመለክ ነበር ማለት ነው፡፡

በሀገራችን ብዙ ወላጆች ለልጆቻቸው በቀጥታ ጸኃይ ወይንም ከጸኃይ ጋር የተያያዘ ስም ማውጣት ያዘወትራሉ፡፡ ጸኃይ፣ጸኃዬ፣ አለም ጸኃይ፣ ጸኃዩ…ወዘተረፈ

እንግዲህ ጸኃይ እስከ 17ኛው ክፍለ ዘመን ድረስ አምላክነቷ እየቀረ ቢመጣም ፀአዳ እንደሆነች መታመኑ ግን እንደቀጠለ ነበር፡፡ በዚህ ጊዜ ታድያ አንድ የስነፈለክ አዋቂ ፍሎሬንስ ከተማ ላይ ይነሳና ቴሌስኮፕን ይሰራል፡፡ በዚህ አዲስ በፈጠረው ነገር ጸኃይን ሲመለከታት ነገር መጣ! ምንም እድፍ የሌለባት ተብላ ትታመን በነበረችው ጸኃያችን ላይ በርካታ ጥቋቁር ነቁጦች (ስፖትስ) ተመለከተ፡፡ (ዝኒ ከማሁ)

    ለካስ ጸኃይ ፀአዳ አይደለችም! ይኸው እድፎች አሉባት፣ እዚህም እዚያም፡፡

ይህ ግኝት እንግዲህ ለፍልስፍና ትልቅ አብዮት ነበር፣ እንዲሁም ለሳይንስ፡፡ ጋሌሊዪ በደንብ አትኩሮ ሲመለከት እነዚያ ጥቋቁር ነቁጦች በጸኃይ ምድር ላይ ሲንቀሳቀሱ ተመለከተ፣ በእርግም እየተሽከረከሩ ነው፡፡ ቀጥሎ በሚመጡት አመታት ሌሎች የጸኃይ ምስጢሮችም እንዲሁ እየተገለጡ መጡ፡፡ ይህ የጋሌሊዮ ጋሌሊይ ግኝት ስለጸኃይ ፍጥረት ለማወቅ ከፍተኛ ጉጉትን ቀሰቀሰ፡፡ ይሁን እንጂ የስነፈለክ ጠበብቱ በጸኃይ ኃይለኛ ነጸብራቅ ምክንያት ብዙም ለማየት እና ለማወቅ አልቻሉም፡፡

ሆኖም ስለ ጸኃይ ጥያቄዎችን አላቆሙም፡፡ የጸኃይ ነቁጦች ምንድን ናቸው? ሌሎች ነገሮችስ ይኖሩ ይሆን? የጸኃይ ኃይል ምንጩ ምንድነው? ቀስ በቀስ ሳይንቲስቱ አንድ ነገር አስተዋሉ፡፡ በየአስር አመት በግርድፉ ስድስት ጊዜ፣ በአለም ላይ በተወሰነ ቦታ፣ጸኃይ በጨረቃ ትከለላለች፡፡ የጸኃይ ግርዶሽም ይሆናል፡፡ በዚህን ጊዜ የጸኃይ ነጸብራቅ ሳያስቸግር ጸኃይን በልዩ መነጽር መመልከት ይቻላል፡፡ ቢያንስ ዙርያዋን፡፡(ዝኒ ከማሁ)

ነገሩ እንዴት መሰላችሁ የጸኃይ ዙርያ የመሬትን አንድ መቶ ጊዜ ይተልቃል፡፡ ጨረቃ ደሞ ከምድርም ያነሰች፣ ማለት ዙርያ ስፋቷ  የመሬትን አንድ አራተኛ ብቻ  ነው የሚያክለው፡፡ ይህ ማለት የጨረቃ ዙርያ ስፋት ከጸኃይ አራት መቶ ጊዜ ያንሳል፡፡ ነገር ግን እዚህ ላይ የሚገርም የተፈጥሮ ግጥምጥሞሽ ይከሰታል፡፡ ምንድነው እሱ? ከጨረቃ ጸኃይ ድረስ ያለው ርቀት ከምድር እስከ ጨረቃ ካለው ርቀት አራት መቶ ጊዜ ይረዝማል፡፡ ስለዚህም አንድ ላይ ስናያቸው ጨረቃ እና ጸኃይ ከሞላ ጎደል እኩል ዙርያ (ሰርከምፍራንስ) አላቸው፡፡ ስለዚህም  ጨረቃ በምድርና በጸኃይ መካከል በምትሆንበት ገዜ፣ ለጥቂት ደቂቃዎች፣ በተወሰነ የአለም ክፍል፣ ጸኃይን ሙሉ በሙሉ መሸፈን ትችላለች፡፡(ዝኒ ከማሁ)

የጸኃይ ግርዶሽም ይሆናል!

 ሙሉ የጸኃይ ግርዶሽ የጸኃይን ጠርዝ ማለት ኮሮናን እንድናይ ያስችለናል፡፡ሌላ ጊዜ የጸኃይ ጠርዝ (ኮሮና) በጸኃይ ነጸብራቅ እንዳይታይ ይሆን ነበር፡፡ ስለዚህም የስነፈለክ ሳይንቲስቶች ኮሮናውን ለማየት የጸኃይ ግርዶሽ አለ በተባለ ቦታ ሁሉ አህጉሮች እና ሀገራትን አቋርጠው ይሄዱ ነበር፡፡ በኮረና ተከባ ስትታይ ጸኃይ ጥቁር የእሳት ኳስ ትመስላለች፡፡ በኮረናው ውስጥ የሚነዱ ደመናዎች ይታያሉ፡፡ መቸም የሚታየው ነበልባል ስለሆነ እሳቱ ከጸኃይ ምድር ላይ የተነሳ መሆን አለበት፡፡ ስለዚህም ጸኃይ ንቁ /ተንቀሳቃሽ ማለትም አክቲቭ ነች፡፡

   በጸኃይ ግርዶሽ ወቅት ምን እናያለን?

በዚህ ግዜ በዋናነት ጎልቶ የሚታየው ነገር ፕሮሚናንስ ይባላል፡፡ ፕሮሚናንስ ከጸኃይ ተነስቶ ወደ ላይ የሚጎን ቢጫ እና ቀይ ነገር ነው፡፡ በጸኃይ ግርዶሽ ወቅት የጸኃይ ዙርያ በትንሹ በሚምቦገቦግ እሳት መሰል ነገር የተከበበ ሲሆን፣ ፕሮሚናንስ ከዚህ ኮሮና ከሚባለው የጸኃይ ዙርያ ተስፈንጥሮ ወደ ላይ የሚጎን ቢጫ እና ቀይ ነገር ነው፡፡ ከታች ስዕሉ የበለጠ ይገልጸዋል፡፡ (ዝኒ ከማሁ)

ይሁን እንጂ የጸኃይ ግርዶች በስንት ጊዜ አንዴ የሚገጥም እናም እጅግ በዛ ቢባል ከጥቂት ደቂቃዎች በላይ የማይቆይ ክስተት ነው፡፡ ይህ ደሞ ለሳይንቲስቶቹ ጸኃይንም ሆነ ፕሮሚናንስን ለማጥናት የሚሰጠው እድል ውሱን ነው፡፡    

ፕሮሚናንስ ይህ ነው፡፡ ከጸኃይ ተነስቶ ወደ ላይ የሚጎን ቢጫና ቀይ ነገር ከ ጌቲ ምስሎች

ጋሌሊዮ ጋሌሊይ ቴሌስኮፕን በፈለሰፈ በሁለት መቶ አመቱ ገደማ፣ አባ አንጄሎ ሳኪ የተባሉት የቫቲካን ዋና የስነፈለክ ሊቅ አንድ አዲስ ግኝት ለአለም አበረከቱ፡፡ ይህም ሰቴርዮስኮፒ የሚባል አዲስ የሳይንስ ዘርፍ ነው፡፡ እንግዲህ ሰቴርዮስኮፒ ልዩ መሳርያ በመጠቀም በፎቶ፣ ፊልም ወይም ሌላ ምስል ላይ ለእያንዳንዱ አይን የተለያየ ምስል የማየት ኢምፕሬሽን መፍጠር ነው

ኦሪጅናል ስቴሪዮስኮፒክ ካርድ ይህን ይመስላል © The National Portrait Gallery, London

የአባ አንጄሎ ሳኪ ስቴሪዮስኮፒ የጸኃይን ብርሀን በተለያዩት ቀለሞቹ ይሰነጣጥቅና የአንዱን ክፍል (ሪጅን) ብቻ አጉልቶ ያሳያል፡፡ አሁን እንግዲህ ጸኃይን አለ ኮሮናዋ (ጠርዝ) ለማየት ተቻለ፡፡ ማለት የጸኃይ ነጸብራቅ የተቀረውን ጸኃይ አካል እንዳናይ አያደርገንም፡፡ ስለዚህም ስቴርዮስኮፒ የጸኃይን ገጽታ በሚገርም መልኩ ለማየት አስቻለ፡፡ (ዝኒ ከማሁ)

አሁን የጸኃይ ብርሀን ነጸብራቅ ስለማያስቸግረን ብዙ ነገር ማየት እንችላለን፡፡ የጸኃይን ጠርዝ ብቻ ሳይሆን ምድሩንም በደንብ ይታይ ጀመር፡፡ ስለዚህም ሳይንቲስቶች የጸኃይን ገላ ማየት ጀመሩ፡፡ የጋሊሌዮን ሰንሰፖትስ በቅርቡ በደንብ አዪዋቸው፡፡

የጸኃይ ገላ በሳይንቲስቶቹ ፊት ይፍለቀለቅ ጀመር፡፡ አሁን ፊት ለፊት የሚያዩዋቸውን ንጥረ ነገሮች (ኬሚካልስ) መመዝገብ ያዙ፡፡ በስፔክትረሙ የሚታዩት ጥቁር ቋሚ መስመሮች (ባንድስ) የሀይድሮጂን፣ ካልሲየም፣ እና ብረት መኖርን ያሳያሉ፡፡ እናም ወዲያው ምድር ላይ ጨርሶ የማያውቁትን ንጥረ ነገር አገኙ፡፡ ስሙንም በጸኃይ አምላክ ስም ሂሊዮስ አሉት፡፡ ሂሊየም፡፡ ትልቁ ግኝት የተመዘገበው ግን አባ ሳቺ ሰቴርዮቴስኮፓቸውን ወደ ከዋክብት አዙረው መመልከት ሲጀምሩ ነው፡፡ ወዲያው ፓተርኑ (ስርአተ ጥለት) ግልጽ ሆነላቸው፡፡ ንጥረ ነገሮቹ (ኬሚካልስ) ከ ጸኃይ ጋር ተመሳሳይ ናቸው፡፡ ትልቁ ዳቦ ሊጥ ሆነ! የአጥናፈ ሰማይ (ዩኒቨርስ) ዋና እንቆቅልሽ ተፈታ፡፡ (ዝኒ ከማሁ)

ጸኃያችን ኮከብ ነች !

ጸኃይ ቅርቧ ኮከብ ስትሆን፣ ከዋክብቱ ደሞ የሩቅ ጸኃዮች ናቸው፡፡ እንግዲህ ከዋክብት የአጽናፈ ሰማይ አይነተኛ አካል ናቸው፡፡ ልክ ሴሎች የሰውነታችን ዋና አካል እንደሆኑ፡፡ ስለዚህም ጸኃይን ማጥናት ማለት አንድ መደበኛ ኮከብን እንደማጥናት ነው፡፡ ይህ ደሞ የአጥናፈ ሰማይን ሁኔታ ለማጥናት ቀላሉ መንገድ ነው፡፡

የጸኃይ አይነተኛ ክፍሎች

የጸኃይ ምድር (ሰን ሰርፌስ)

ከመሬት የምናየው የጸኃይ ክፍል (እኛ የጸኃይ ገጽታ ወይንም ሰርፌስ የምንለው) ፎቶስፌር ይባላል፡፡ በእርግጥ ጸኃይ ገጽታ (ሰርፌስ) የላትም ምክንያቱም ጸኃይ የፕላዝማ ኳስ ስለሆነች፡፡ ይህ ክፍል ፎቶስፌር የተባለው ለኛ የሚታየን ብርሀን የሚገኝበት ስለሆነ ነው፡፡ ፎቶስፌርን እኛ ሰርፌስ እንበለው እንጂ ሳይንቲስቶች የከባቢ አየሩ የመጀርያ ንብርብር (ሌየር) ነው የሚሉት፡፡

ይህ ንብርብር ሁለት መቶ አምሳ ማይል ይደርሳል፣ሙቀቱ ደሞ እስከ አምስት ሺ አምስት መቶ ዲግሪ ሴንትግሬድ ነው፡፡ ይህ እንግዲሀ ከፍተኛ ሙቀት ሊመስለን ይችላል ከጸኃይ እንብርት ሙቀት ጋር ሲወዳደር ግን ቀዝቃዛ ነው፡፡ ይሁን እንጂ ሙቀቱ እንደ አልማዝ እና ግራፋይት የመሰሉ የካርቦን ዘሮችን መስራት ይችላል፡፡ አብዛኛው የጸኃይ ብርሀን ከፎቶስፌር ተነስቶ ነው ወደ ሕዋ የሚጎነው፡፡ ቀጥሎ የምናገኘው የጸኃይን አትሞስፊር ሲሆን እዚህ ላይ ሰን ስፖትሰ፣ኮሮና፣ ሰን ፍሌየርስ፣ ፐሮሚናንስ፣ ኮሮናል ማስ ኢጀክሽን እና የመሳሰሉት ክስተቶች የሚታዩበት ነው፡፡ (NASA Science)

በጸኃይ ግርዶሽ ወቅት የሚታየው ኮሮና* Adobe Stock

    አትሞስፊር

ኮሮና የጸኃይ አትሞስፊር ከፍተኛው ክፍል ነው፡፡ ከሚታየን የጸኃይ ገጽታ ብዙ ሺ ኪ/ሜትሮች ይነሳል፡፡ቀስ በቀስም ኮሮና ወደ ጸኃይ ነፋስነት ይቀየራል፡፡ ኮሮና በየጊዜው ቦታውን እና ቅርጹን ይቀያይራል፡፡ በጣም የሚገርመው የኮሮና ባህርይ ከጸኃይ ገጽታ የበለጠ ሙቀታማ መሆኑ ነው፡፡ (UCAR – center for science education: The hidden Corona, Suns atmpsphere)

ምስል ናሳ፡፡ሰንስፖቶቹ ጥቁር ነቁጥ ሆነው የሚታዩት ናቸው፡፡

ሰንስፖት በቢጫው የጸኃይ ገላ ላይ ጥቁር ጉድጓድ መስለው ይታያሉ፡፡ልክ ወደ ምስጢራዊ ክፍል እንደሚያሳይ መስኮት፡፡ ሰንሰፖቶች ጥቁር መስለው የሚታዩን ከአካባቢው ያነሰ ቅዝቃዜ ስላላቸው ነው፡፡ (ናሳ 16/08/2024)

ሰን ፍሌይርስ እነዚህ ደሞ በጸኃይ ላይ ኃይል (ኢነርጂ) በድንገት ሲፈነዳ የሚፈጠር ክስተት ነው፡፡ ይህም እንግዲህ በሰንስፖት አካባቢ በሚፈጠር የተቆላለፈ ማግኔቲክ ፊልድ (መግነጢሳዊ መስክ) ነው፡

ሰን ፍሌይርስ

   ማግኔቶስፌር

እንግዲህ የጸኃይ ማግኔቶስፌር የጸኃይ መግነጢሳዊ መስክ ወይም ማግኔቲክ ፊልድ ሲሆን ይህም በመላው ስልተ ጸኃይ (ሶላር ሲስተም) ላይ የተንሰራፋ ነው፡፡ የጸኃይ መግነጢሳዊ መስክ በጸኃይ ነፋሳት ተሸካሚነት የሚንቀሳቀስ ነው፡፡ በጸኃይ መግነጢሳዊ መስክ የሚፍለቀለቀው የህዋ ክፍል ሂሊዮስፌር ይባላል፡፡ (NASA Science (.gov)

የጸኃይ ባህርያት

የጸኃይ ገጽታ ትርምስ የበዛበት ቦታ ነው፡፡ በኤሌክትሪክ የተመሉ (ኤሌክትሪካሊ ቻርጅድ) የሆኑ ጋዞች አሉት፡፡ እነሱም ሀይለኛ የማግኔቲክ ሀይል አካባቢን ይፈጥራሉ፡፡ እነዚህም አካባቢዎች መግነጢሳዊ መስክ (ማግኔቲክ ፊልድ) ይባላሉ፡፡ የጸኃይ ጋዞች ዘወትር ተንቀሳቃሽ ናቸው፣ በዚህም የመግነጢሳዊ መስኩን እየሳቡ መልሰው ይለጥጡታል፡፡ ይህም ከፍተኛ እንቅስቃሴን በጸኃይ ገላ ላይ ይፈጥራሉ፡፡ የጸኃይ እንቅስቃሴ የሚባለው እንግዲህ ይህ ነው፡፡ (ዝኒ ከማሁ)

 ሆኖም ይህ እንቅስቃሴ ሁሌም ተመሳሳይ አይደለም፡፡ አንዳንዴ በጣም ይተራመሳል፡፡ አንዳንዴም ጸጥ ይላል፡፡ ይህ የእንቅስቃሴ ከፍታና ዝቅታ ደረጃ በደረጃ እየተለዋወጠ የጸኃይ ዑደቶችን ይፈጥራል፡፡ ይህ ተለዋዋጭ የጸኃይ ዑደት በግርድፉ በየ 11 አመቱ የሚመጣ ነው፡፡ በዚህም ጊዜ የጸኃይ እሳታማ አውሎ ነፋሶች ይበረታሉ፣ በምድር ላይም ተጽዕኖ ይኖራቸዋል፡፡ (ዝኒ ከማሁ)

በ 1973 ስካይላብ የተባለች የሶላር ላቦራቶሪ ወደ ጸኃይ ተላከች፡፡ ጊዜ ወስዳ ጸኃይን በደንብ ልታጠና፡፡ ለዘጠኝ ወራት ያህል የተለያዩ አስትሮኖቶች በተከታታይ ጥናት አካሄዱ፡፡ ጸኃይን በደንብ ለማየት የሚያግድ ከባቢ አየር በሌለበት የጸኃይ ጥናት የምር ተካሄደ፡፡ በዚህን ወቅትም አስትሮኖቶቹ ከ 160 000 በላይ የጸኃይ  ምስሎችን አነሱ፡፡ በዚህም ብዙ ነገር አገኙ፡፡ ከነዚህም አንዱ የኮሮናል ማስ ኢጀክሽን ነው፡፡ ይህ ከሶላር ፍሌር እጅግ በበዛ መጠን ቅንጣቶች (ፓረቲክልሰ) ከጸኃይ ገላ ወደ ላይና ውጪ ሲፈነዱ ነው፡፡ (ቢቢሲ ዶክ)

ኮሮናል ማስ ኢጀክሽን፣ የተቆጣች ጸኃይ ይህን ትመስላለች  Space.com

እነዚህን አካባቢ አንቀጥቅጥ ፍንዳታዎች ምን ፈጠራቸው? የዚህ ጥያቄ መልስ መልሶ ወደ ሰንሰፖትስ ይወስደናል፡፡ በ ሀያኛው ክፍለዘመን መግቢያ ስፔከትሮስኮፒ ን የሚያግዝ አንድ ስፔክቶግራፍ የሚባል መሳርያ ተሰራ፡፡ ይህ መሳርያ የጸኃይን ብርሀን በኢነርጂ ኮምፖናንት ከፋፍሎ የሚያሳይ ነው፡፡ በነዚህ መሳርያዎች በመታገዝ በተደረገው ምርምር ሰንሰፖቶች የሚፈጠሩት በማግኔቲክ ዲስቶርቴሽን እንደሆነ ተደረሰበት፡፡  በዚህም ሰንስፖትስ አካባቢ የሚፈጠር ማግኔቲክ ዲስቶርቴሽን የጸኃይ ኃይለኛ አውሎ ነፋሶችን ይፈጥራል፡፡ እነዚህ ሰቶርምስ (አውሎነፋሶች) በጸኃይ ገጽ ያለውን ፕላዝማ አፈንድተው ብዙ ሺ ኪ/ሜትሮች ወደ ሰማይ ካጎነኑት በኃላ ተመልሶ ወደ ሚንቀለቀለው የጸኃይ ምድር (ሰርፌስ) ላይ ያሳርፈዋል፡፡ ከነዚህም ተያይዞ የ ጸኃይ ማግኔቲክ ሰቶርም ይነሳል፡፡ (ቢቢሲ ዶክ)

አነዚህ ከጸኃይ ንፋሶች በተገናኘ የሚነሱት ማግኔቲክ ስቶርምስ በይዘታቸው በኤሌክትሪክ የተመሉ ቅንጣቶች (ኤሌክትሪካሊ ቻርጅድ ፓርቲክልስ) ናቸው፡፡ እነሱም ከመሬት መግነጢሳዊ መስክ ጋር ሲገኛኙ የሰሜን ነፋሳትን ይፈጥራሉ፡፡ የመሬት መግነጢሳዊ መስክ ከጸኃይ የሚመጡ በኤሌክትሪክ የተመሉ ቅንጣቶችን የያዙ የጸኃይ ንፋሳትን ሲከላከል የሚኖረው ፍጭት ነው እንግዲህ አውሮራ ወይም የሰሜን ብርሀን የተባለውን ክስተት የሚፈጥረው፡፡ የሰሜን ብርሀን በዋልታዎች ላይ የመሬት መግነጢሳዊ መስክ መሬትን ከጸኃይ ነፋሳት ሲከላከል በሚኖረው ፍጭት የሚፈጠር የኅብረ ብርሀናት ዳንስ ነው፡፡ ለማየት እጅግ ስለሚያስደስት አገር ጎብኚዎች አውሮራ በሚበዛበት ወቅት (ሲዝን) ወደ ኖርዌይ ይጎርፋሉ፡፡

የአውሮራ ወይም የሰሜን ብርሀናት

የጥንት ሰዎች የሰሜን ብርሀናት እና እነሱም ሲታዩ የሚፈጠው ድምጽ፣የሟች ወታደሮች ነፍሳት በሰማይ ሲፋለሙ የሚፈጠር ነው ተብሎ ይታመን ነበር፡፡ ከብዙ ምርምር በኃላ ነው አውሮራዎች በጸኃይ ነፋሳት ሳቢያ የሚፈጠሩ ክስተቶች እንደሆኑ የተደረሰበት፡፡ ሆኖም ብዙ ሳይንቲስቶች ከጸኃይ የስበት ሀይል አምልጦ የሚፈተለክ ነገር መኖሩን ይጠራጠሩ ነበር፡፡ ሆኖም ዘግይቶ ይህ ሊሆን እንደሚችል ተደረሰበት፡፡

ናሳ በ 27 ኦገስት 1962 የማሪነር ሁለት የጠፈር መንኮራኩርን ወደ ጠፈር አመጠቀ፡፡ ማሪነር ሁለት ወደ ሌላ ፕላኔት የተላከች የመጀመርያዋ የጠፈር መንኮራኩር ነች፡፡ በተሳካው ተልዕኮዋ ከደረሰችባቸው ዋና ግኝቶች አንዱ፣ የጸኃይ ንፋስ ከጸኃይ አልፎ እንደሚበር ማረጋገጧ ነው፡፡ (NASA Jet Propulsion Laboratory (.gov) missions › mariner-2)

የጸኃይ እምብርት (ኮር)

 የጸኃይ እምብርት ከጸኃይ አካላት ሁሉ እጅግ የሞቀው ክፍል ነው፣ ሙቀቱ እስከ 15 ሚሊዮን ዲግሪ ሴንቲግሬድ ይደርሳል፡፡ ወደ 138000 ኪ/ሜ ውፍረት አለው፡፡ይህ ሁሉ ሙቀት ሀይድሮጂን ወደ ሂሊየም  የሚቀየርበት (fussed) ሲሆን፣ የጸኃይን ሀይል እና ሙቀት የሚፈጥረው ሂደት ይህ ነው፡፡ (NASA Science)

አንዳንድ ነጥቦች ስለ ጸኃይ

እኛ እዚህ ምድር ላይ ቀንና አመቱን የምንለካ ከጸኃይ አንጻር ነው፡፡ ምድራችን በራሷ ዛቢያ አንዴ ስትዞር አንድ ቀን ሆነ እንላለን፡፡ በጸኃይ ዙርያ አንዴ ተሸከርክራ ስትጨርስ ደሞ አንድ አመት፡፡

የጸኃይ ቀን እና አመትስ ምን ያህል ይሆን? ይህን ጥያቄ ልጅ ሆኜ ለቄስ አስተማሪዬ አባ ፍስሐ ባቀርብላቸው፣ አንዴ በመስቀላቸው ኮርኩመውኝ፣ አርፈህ አውደ ንባቡን ተወጣ ነበር የሚሉኝ፡፡

የጸኃይ አንድ ቀን ምን ያህል ርዝመት አለው የሚለውን ለማብራራት ትንሽ ይከብዳል፡፡ ጸኃይ የተሰራችው ፕላዝማ ከተባለ በኤሌክትሪክ በተሞላ ልዕለ ሞቃት ጋዝ ነው፡፡ ፕላዝማ ታድያ በተለያዩ የጸኃይ ክልሎች በተለያየ ፍጥነት ነው የሚሽከረከረው፡፡ ስለዚህ ጸኃይ በራሷ ዛቢያ ለመዞር፣ በመቀነቷ (ኢኩዌተር) ላይ ከሆነ 25 የመሬት ቀናት ይፈጅባታል፡፡ በዋልታዎቿ አካባቢ ከሆነ ደሞ ሰላሳ ስድስት ቀናት ይወስድባታል፡፡ (ዝኒ ከማሁ)

 ይቺ ቢጫ የብርሀን ኳስ፣ ይቺ ከኛ 150 ሚሊዮን ኪ/ሜ የምትርቀው ኮከባችን በዙርያዋ ስምንት ፕላኔቶች፣ ቢያንስ አምስት ሙት ፕላኔቶች (ድዋርፍ)፣ በአስር ሺዎች የሚቆጠሩ አስትሮይዶች፣ እና ሶስት ትሪሊዮን ኮሜቶች እና በረዷማ አካላት ይሽከረከሯታል፡፡ በቅርብ የሚያዋስናት ባለ ሶስት ከዋክብት ስታር ሲስተሙ አልፋ ሳንታሪ ነው – ሶስቱ በዚህ የስታር ሲስተም የተጠቃለሉት የጸኃይ ጎረቤት ከዋክብቶች ደሞ

ከላይ እንደነገርናችሁ ጸኃይ ዙርያዋን እየተሽከረከሩ የሚያጅቧት እጅግ ብዙ የስልተ-ጸኃይ አካላት እንዳሏት ሁሉ እሷም ይህን ሁሉ አጀብ አስከትላ የሚልኪ ዌይን ጋላክሲ ማዕከል ትዞራለች፡፡(ዝኒ ከማሁ)

አየንልሽ አየንልሽ

ይኸው ብቻ ነው ወይ አጀብሽ?

እያልን በሰርግ ጊዜ እንደምንዘፍነው ሳይሆን ጸኃይ አጀቧ ብዙ ነው፡፡

 እንግዲህ ጸኃያችን የምትሽከረከረው በሰዐት ሰባት መቶ ሀያ ሺ ኪ/ሜ ቢሆንም፣ አንድ ሙሉ ሽክርክሪት ለማረግ ሁለት መቶ ሰላሳ ሚሊዮን አመታት ይፈጅባታል፡፡ ስለዚህ አንድ ቀን በጸኃይ የኛ 25 ወይም 36 አመት ሲሆን፣ የጸኃይ አንድ አመት ደግሞ የኛ ሁለት መቶ ሰላሳ  ሚሊዮን አመት ነው፡፡

የጸኃይ ተጠቃሽ ባህርያት

በሁለት ዲሰምበር 1972 የአውሮፓው የህዋ ድርጅት እና ናሳ በመተባበር ሶሆ የሚባል የጠፈር መንኮራኩር ጸኃይን እንዲያጠና ወደ ጠፈር አመጠቁ፡፡ የሚገርመው ነገር የዚህ መንከኮራኩረ መሳርያዎች የጸኃይን ገጽታ መመልከት ብቻ ሳይሆን የጸኃይን እምብርት መስማት የሚችሉ ነበሩ፡፡ የጸኃይን እምብርት ዘልቀህ መመልከት አይቻልም፡፡ ነገር ግን መስማት ተቻለ፡፡ በእምብርቱ ውስጥ የሚገኙ ድምጾችን በመስማት የጸኃይን ውስጣዊ መዋቅር መረዳት ይቻላል፡፡ (ቢቢሲ ዶክ)

 በዚህ መንኮራኩር አማካይነት እንደታወቀው፣ የጸኃይ ገጽ እና እምብርቱም ይተነፍሳሉ (heaving)፣ በየስድስት ስኮንዱ ጠቅላላ የጸኃይ (ስታር) አካል ወደ ውስጥ እና ወደ ውጭ ይተነፍሳል፡፡ የእምብርቱ ጋዝማ ውቅያኖሶች በጥልቀት ወደ ውስጥ ይተነፍሳሉ በዚህም የተወሳሰቡ ትናንሽ ሞገዶች (ሪፕልስ) በገጽታው የተረማመሳሉ፡፡ እንዚህም የውስጡን መዋቅር ፍንጭ ይሰጡናል፡፡ (ዝኒ ከማሁ)

እንደማንኛውም ኮከብ ሁሉ፣ የጸኃይ እምብርት (ኮር) የንጥረ ነገሮች (ኬሚካልስ) ሁሉ ፋብሪካ ነው ህይወትንም ጨምሮ፡፡ ማለት ከሌላውም በተጨማሪ ለህይወት መሰረታዊ የሆኑ ንጥረ ነገሮች ሁሉ የሚፈበረኩት በጸኃይ እምብርት ነው፡፡ የጸኃይን (የኮከብን) መሰረታዊ ፊዚክስ ማወቅ መሰረታዊ ነገር ነው፡፡ ምክንያቱም በ ኮከቦች የሚኖረው ፊዚክስ ከፕላኔቶች ፊዚክስ ጋር ተመሳሳይ ስለሆነ፡፡ (ዝኒ ከማሁ)

 አሁን ሶሆ የጸኃይን የላይኛው ክፍልን ማጥናት ጀምራለች፡፡ አዲስ የጸኃይ ገጽታ ክስተትንም አውቀናል፡፡ ከሶላር ፍሌር በኃላ ሺ ኪ/ሜትሮችን የሚሸፍን የመንቀጥቀጥ ክስተት ይፈጠራል፡፡ የነዚህን መንቀጥቀጥ ድምጾች ስለ ጸኃይ የውጭ ገጽታ ብዙ መማር እንችላለን፡፡ አሁን በተመሳሳይ ከድምጾቹ ተነስተን ውስጣዊውን የጸኃይ ሁኔታ ለማጥናት ይቻላል፡፡

ሁሉም ኮከብ ማለት ይቻላል እምብርት (ኮር) አለው፡፡ በእምብርቱም ኑክሌር ኢነርጂን ይፈጥራል፣ በዚህ ሂደትም አንድን ማቴርያል ወደ ሌላ ይለውጣል (ትራንሚዩቲንግ ኤለመንትስ)፡፡ በዚህም ሂደት የአጽናፈ ሰማይ ዋልታ እና ማገር የሆኑትን ከባባድ ኤለመንቶችን ይገነባሉ፡፡ ቀደም ብለን እንዳልነው የኮከብ ፊዚክስ እና የመሬት ተመሳሳይ ነው፡፡ የኮከብን መዋቅር በደንብ አወቅን ማለት የአጽናፈ ሰማይን መዋቅር እንዲሁ ተረዳን ማለት ነው፡፡ (ዝኒ ከማሁ)

ጸሀያችን እንዴት ተፈጠረች?

በመጀመርያ በአጽናፈ ሰማይ የተከማቹት ንጥረ ነገሮች (ኤለመንትስ) ሀይድሮጂን እና ሂሊየም ብቻ ነበሩ ፡፡ በአስራ ሁለት ቢሊዮን አመታት ከዋክብት እነዚህን ንጥረ ነገሮች ወደ ተለቁ፣ የተራቀቁ ንጥረ ነገሮች ቀየሯቸው፡፡ የኛም ጸኃይ ከዚህ ሂደት የተገኘች ናት፡፡ የዛሬ አራት ነጥብ አምስት ቢሊዮን አመት በፊት በጋላክሲያችን ጠርዞች ላይ የነበረ እጅግ ትልቅ ኮከብ (በሱፐር ኖቪ) መኖሩ አብቅቶ ተበተነ፡፡

የዚህ ግዙፍ ኮከብ ፍንዳታ በእምብርቱ የነበሩትን ንጥረ ነገሮች ወደ አካባቢው ጠፈር በተናቸው፡፡ እንዚሀ ልዕለ ሞቃት (ሱፐር ሂትድ) ሲሊከን፣ ብረትና ሌሎችም በአካባቢው በነበረው አፈርና ጋዝ ላይ ጭነቱን ስላበዙት ስብስቡ ጭነቱን መሸከም አቃተው፣ እነዚህ ከባባድ ንጥረ ነገሮች ወደ ማዕከሉ ተስበው ትልቅ የክሚካል ሪአክሽን አስነሱ፡፡ ፍንዳታም ሆነ፡፡ ጸኃያችን ከዚህ ፍንዳታ (ኬሚካል ሪአክሽን) ተስፈንጥራ ህያው ሆነች፣ ተፈጠረች፡፡ ከፍንዳታው የተረፈው ማቴርያልም   በአክሬሽን ሂደት ፕላኔቶችን ፈጠረ፡፡ (ዝኒ ከማሁ)

ቅዱስ መጽሀፍ ‘’ኦ አዳም! መሬት አንተ፡፡ ውሰጠ መሬት ትገብዕ’’ እንዲል፡፡ እኛ የኮከብ አፈር ነን ፡፡ ላለፉት አራት መቶ አመታት ሳይንስ የጸኃይን ዙርያ ሽፋኖች እየገላለጠ ኮከብን አገኘ፡፡ ይህ ፕላኔቶችን ያበጀው  የስነፍጥረት ካልኩለስ ሞተር እኛንም ፈጠረን፡፡ አያት ቅምአያቶቻችን ጸዐዳ የሆነች የብርሀን ዲስክ አዩ፡፡ ሳይንስ ደሞ እነሱ ከሚገምቱት እጅግ ኃይለኛ የሆነ ኢንቲቲን ገለጸልን፡፡ (ቢቢሲ ዶክ)

ለማንኛውም አስተያየት ካላችሁ itaye4755@gmail.com ላይ እንገኛለን

ምንጭ

BBC Documentary, THE PLANETS, 1999

 NASA Science (.gov) Our Sun: Facts – NASA Science)

 NASA 16/08/2024

NASA Jet Propulsion Laboratory (.gov) missions › mariner-2

© The National Portrait Gallery, London

UCAR – center for science education: The hidden Corona, Suns atmpsphere

Add post to Blinklist Add post to Blogmarks Add post to del.icio.us Digg this! Add post to My Web 2.0 Add post to Newsvine Add post to Reddit Add post to Simpy Who's linking to this post?

ጊዜ ቤት እንጫወት 28 Feb 2:58 AM (14 days ago)

በልጅነታችን ጊዜ ቤትን በቃሉ የሚያውቅ ተማሪ ይደነቅ ነበር፡፡ አንደኛ ደረጃ ሆነን ማለቴ ነው፡፡ እኔ ባደግሁበት አዋሽ ሰባት ኪሎ ከተማ የጣቶቻቸውን ሰረዞች በመነካካት ከጊዜ ቤት ጥያቄዎች ወዲያውኑ መልስ የሚሰጡ ልጆች ነበሩ፡፡ እነሱም የአቶ ሰቃፍ ዑመር ልጆቻች ናቸው፡፡ ዘዴውንም የሚያስጠናቸው ራሱ ሰቃፍ ነበር፡፡ በዚህም ለአቶ ሰቃፍም ለልጆቹም የ’’ብሪሊያንትነት’’ ማዕረግ ሰጥተናቸው ነበር፡፡

በዚህ መጣጥፍ ነገሬ ብለን ልናተኩርበት የፈለግነው የሳይንስ ዘርፍ ሂሳብ ነው፡፡ በተለይ ልጆቻችንን በአንደኛ እና መለስተኛ ሁለተኛ ደረጃ ለምናስተምር ወላጆች፣ ልጆቻችንን ከወዲሁ ስለ ሂሳብ ግንዛቤ እንዲኖራቸው እና እንዲወዱት ማድረግ እንዳለብን አስረግጠን ማሳሰብ እንወዳለን፡፡

አንድን ችግረኛ ሰው አንድ አሳ ብንሰጠው የአንድ ቀን ረሀቡን ልናስታግስለት እንችላለን፡፡ አሳ ማጥመድ ብናስተምረው ግን ለዘለቄታ ርሀቡን እናስወግድለታለን፣ የሚል የቻይኖች ይትበሀል አለ፡፡ ይህን ይትበሀል ወደ ሂሳብ ትምህርት ወስደን ብናሻሽለው እንደሚከተለው ይነበባል፡፡

‘’የልጅህን የሂሳብ ቤት ስራ ብትሰራለት የአንድ ቀን የቤት ስራ ግዴታውን ተወጣህለት ማለት ነው፡፡ ሂሳብን እንዲወድና በሂሳብ ጎበዝ እንዲሆን ብትገፋፋው ግን በሁሉም ትምህርቶች ጎበዝ እንዲሆን ታደርገዋለህ’’

ሂሳብ የትምህርቶች ሁሉ ቁልፍ ነው፡፡ ገና ከአንደኛ ደረጃ ጀምሮ በሂሳብ ጎበዝ የሆነ/የሆነች ልጅ እያደገ ሲመጣ በሁሉም ትምህርቶች ጎበዝ ይሆናል፡፡ የወደፊት ህይወቱም ስኬታማ የመሆኑ እድል በብዙ እጥፍ ይጨምራል፡፡

ሂሳብን ከባድና አስቸጋሪ ነገር አድርገን ከወሰድነው በጣም ተሳስተናል፡፡ በእርግጥ በጥልቀት ማሰብን ለማይወድ ሰው የሂሳብ ትርጉም እንደዛ ቢሆን አይገርምም፡፡ ግን ሂሳብን ለልጆች አዝናኝ አድርገን ካስለመድናቸው፣ ትምህርቱ ምን ያህል አስደሳችና ጠቃሚ እንደሆነ ይረዱታል፡፡

እስቲ ሁለት ትልልቅ ሰዎች በልጅነታቸው ሂሳብን እንዴት ይሰሩት እንደነበር እንመልከት

አንድ ቀን፣ የማወቅ ጉጉቱ ከፍተኛ የሆነ እና በአሻንጉሊቶች መጫወት ቀደም ብሎ የያቆመ፣ በትምህርት ጀረጃው ከፍ ያለ ልጅ አጎቱን እንዲህ ሲል ጠየቀው፡፡

‘’አልጀብራ ምንድነው?’’

መሀንዲስ የሆነው አጎትየው ፈገግ አለና የሚከተለውን መልስ ሰጠው

‘’አልጀብራ አዝናኝ(fun) ሳይንስ ነው፡፡ አንድን ነገር ልናውቀው ወይም ልንይዘው ካልቻልን X ብለን እንጠራውና እስክንይዘው ድረስ ፍለጋችንን እንቀጥላለን’’ አለው

ከዚያን ቀን አንስቶ አጎት ያዕቆብ ለወንድሙ ልጅ በየደረጃው እየከበዱ የሜሄዱ የአልጀብራ  ጥያቄዎችን ይሰጠው ጀመር፡፡ ተግዳሮቱን እየወደደው የመጣው ልጅ ሂሳቦቹን አስተካክሎ ይሰራ ገባ፡፡ አጎትየው በበኩሉ የወንድሙ ልጅ፣ ጥያቄዎቹን ለመፍታት ይጣጣር ይሆን? ብሎ እየተጠራጠረ ነበር የቤት ስራዎቹን የሚሰጠው፡፡

ልጁ ግን በየጊዜው የ X ን መልስ እያገኘ፣ ይህም ደስታ እየሰጠው፡፡ የደስታ ስሜቱ ለሚቀጥለው ጥያቄ እያጓጓው እርምጃውን ቀጠለ፡፡

የትንሹ ልጅ ስም አልበርት አነስታይን ይባላል

ይህ የማወቅ ጉጉቱ የት አደረሰው? መልሱን ለናንተ እንተዋለን፡፡

ሌላው፤ ቀደም ባለ ጊዜ በአንድ የጀርመን አንደኛ ደረጃ ት/ቤት እድሜያቸው በሰባት እና በስምንት አመት መካከል የሚገኙ ተማሪዎች በሚማሩበት ክፍል የደረሰ ነገር ነው፡፡ አስተማሪው ለተማሪዎቹ አንድ የክፍል ስራ ይሰጣቸዋል፡፡ የክፍል ስራው ከ 1 እስከ 100 ያሉትን ቁጥሮች ድምር መስራት ነው፡፡

ከአንድ ተማሪ በስተቀር ሁሉም ተጨናንቆ ነጭ ወረቀቱ ላይ አፍጥጦ ነበር፡፡ ይህ ተማሪ ግን ረጋ ብሎ ጥያቄውን ካጤነ በኃላ ወዲያው ምጥጥኑ (symmetry) ገባው፡፡ ቁጥሮቹን በጥንድ፣ የመጀመሪያውን ከመጨረሻው፤ ሁለተኛውን ከመጨረሻው ሁለተኛ፣ ሶስተኛውን ከመጨረሻው ሶስተኛ ጋር ማቧደን እና መደመር፡፡ አሁን ሁሉም ተመሳሳይ ውጤት ይሰጣሉ፤ ማለት

1+100 = 101

2+99 = 101

3+98 = 10

በሌላ መልክ ስናስቀምጠው

50 pairs × 101 (the sum of each pair) = 5,050.   (Quara, posted by Alessandro)

ስለዚህ በቀላሉ 50 ጊዜ 101  ወይም 5050 መልሱ ይሆናል ብሎ አስቀመጠ፡፡

ቢንጎ ! መልሱ ትክክል ነበር፡፡ መምህሩ ነገሩን ማመን አቃተው፤ከመልሱ ትክክልነት የተገኘበት ፍጥነት !

በዚያ ክፍል ውስጥ አንድ የወደፊት ሊቅ እንደተገኘ መምህሩ ወዲያው ገባው፡፡

ካርል ፍሬደሪክ ጋውስ

የዚያ ስምንት አመት ተማሪ ልጅ ስም ካርል ፍሬደሪክ ጋውስ ነበር፡፡ ካርል ጋውስ ሲያድግ ስመጥር የሆነ የጀርመን ሂሳብ ሊቅ፤ ስነፈለክ ጠበብት፣ የፊዚክስ ተመራማሪ  እና ለብዙ የሳይንስ መስኮች ብዙ ያበረከተ ሰው ሆነ፡፡ ይህ ሳይንቲስት የጎቲንገን ኦብዘርቫቶሪ ዳይሬክተር እና የስለፈለክ ፕሮፌሰር ሆኖ ከ 1807 እስከሞተበት 1855 ድረስ አገልግሏል፡፡

እንግዲህ ልጆችን በልጅነታቸው በሂሳብ ካጫወቷቸው ሊደርሱበት የሚችሉበትን ከፍታ ከላይ ያስቀመጥናቸው ሁለት ምሳሌዎች አሳይተውናል፡፡

የተከታታይ ቁጥሮችን ድምር ለማግኘት የሚጠቅመው  የአልጀብራ ቀመር

N(n+1)/2 ነው፡፡

 እስቲ መጀመርያ ይህን ቀመር ሳታሳዩ ለልጆቻችሁ እንደ እድሜያቸው መጠን በተመሳሳይ ጥያቄ እየያቀረባችሁ አብራችሁ ለመጫወት ሞክሩ በኔ በኩል ሁለት ጥያቄዎችን ጀባ ብያችኃለሁ

የመጀመርያዎቹ 20 ሙሉ ቁጥሮች ድምር ስንት ይሆናል?

የመጀመርያዎቹ 30 ጎደሎ ቁጥሮች ድምር ስንት ይሆናል?

መልሱን ለኛም በ ኢሜይል ላኩልን

itaye4755@gmail.com

Add post to Blinklist Add post to Blogmarks Add post to del.icio.us Digg this! Add post to My Web 2.0 Add post to Newsvine Add post to Reddit Add post to Simpy Who's linking to this post?

መግቢያ 27 Feb 12:57 PM (15 days ago)

እንዴት ከረማችሁ? ስንክሳራችን እየዳኸች ሶስተኛ ወሯን ያዘች፡፡ አሁን ታድያ እየተላመድን የመጣን ይመስለኛል፡፡ በናንተ በኩል አስተያየታችሁን ለዚሁ በተዘጋጀው ቦታ ብትልኩልን ይበልጥ ለማሻሻል የይረዳናል፡፡ ሰብስክራይብ ብታደርጉም ጥሩ ነው፡፡ ፡፡ ከሶስት እትሞች ካገኘችው ልምድ ተነስታ ከአፕሪል ጀምሮ በቀላል ክፍያ ስትቀርብ የበለጠ አርኪ እንድትሆን ምክራችሁን እና አስተያየታችሁን በጣም፣ በጣም እንፈልጋለን እና አደራችሁን፡፡

የፌብርዋሪ እትም ስድስት መጣጥፎችን ይዛለች፡፡ የመጀመርያው አምድ ቤተሰብና ልጆችን ማዕከል ያደረገ ነው፡፡ እንዲህም ስለተባለ ለሌላው ፋይዳ የለውም ማለት አይደለም፡፡ እንዳው ግን በይበልጥ ትኩረቱ ስለ ሂሳብ ትምህርት ጠቃሚነት እና ልጆቻችንን ገና ከጅምሩ አንደኛ ደረጃ እያሉ ሂሳብን በመዝናኛ መልኩ በማቅረብ እንዲወዱት ስለማድረግ የተዘጋጀ ጽሁፍ ነው ለማለት ነው፡፡

ስለዚህ በዚህ ወር የሳይንስ አምድ ‘’ጊዜ ቤትን እንማር’’ በሚል ፈገግ በሚያደርግ ርዕስ ከጊዜ ቤት ከፍ ያለ ነገር ስለ ሂሳብ አቅርበናል፡፡

የዚህ ወር የአሰሳ አምዳችን በ ‘’ጸኃይ’’ ላይ ያተኩራል፡፡ እቺ በቀን በቀን ሙቀትና ብርሀን በነጻ የምትሰጠን ጸኃያችን ምንድን ናት? እንዴት እና መቼ ተፈጠረች? በውስጧስ ምን ምን ነገሮችን ይዛለች? የጠለቀም ባይሆን ለጠቅላላ እውቀት ያህል እነዚህን ጥያቄዎች በመመለስ ስለ ቅርቧ ኮከባችን ጸኃይ ትንሽ እናትታለን፡፡

የባህል እና ስነጥበብ አምዳችን ስለ አዋሽ ሰባት ኪሎ ከተማ የጀመረውን ትርክት ሶስተኛ ክፍል ያቀርባል፡፡ ይህን አምድ ይበልጥ ለመረዳት ያለፉትን ሁለት  የባህል እና ስነጥበብ አምድ ማንበብ ጠቀሜታ ቢኖረውም፣ በታሪክ ፍሰት የተያያዙ ስላልሆኑ የደረሳቸችሁበትን ማንበቡ ችግር አይኖረውም፡፡

ወዳጆቼ፣ በአሁኑ ዘመን ደጋግመን ከምንሰማቸው ነገሮች አንዱ የመረጃ ቴክኖሎጂ ወይንም INFORMATION TECHNOLOGY (IT) ነው፡፡ ሁሉም ስለሚያውቀው አይ ቲ እንበለው፡፡ ደጋግመን እንደመስማታችን ግን ሰለ ጽንስ ሀሳቡ ጥሩ እውቀት ወይንም መረዳት ያለን ሰዎች ጥቂት ነን፡፡ በዚህ አጭር መጣጥፍ የአይቲን ምንነት እና ታሪክ በአጭር ከቀረበበት መጽኃፍ የበለጠ አሳጥረን እናቀርበዋለን፡፡

ይህን ስራ በአይ ቲ በሳል የሆነ ሰው በአማርኛ ቢያቀርበው ምንኛ በተሻለ፡፡ እስከዚያው ግን የአይ ቲ ን ጽንሰ ሀሳብ ምንነት እና ታሪክ ሁሉም እንዲገባው በቀለለ ሁኔታ እናቀርበዋለን፡፡ ስዚህም የዚህ ወር ከመጻኃፍት አምዳችን ‘’የአይ ቲ አጭር ታሪክ’’ በሚል ርዕስ ይቀርባል

በታሪክ አምዳችን ወደ ህንድ ብቅ ብለን በአለም በትልቅነቱ ወደር ስለሌለው በፈቃደኞች የተገነባ ድርጅት የምንላችሁ ይኖረናል፡፡

በዚህ ወር የአለም አቀፍ ግንኙነት አምድ አንድ ወር ስላለፈው የፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ አስተዳደር ትንሽ እናትታለን፡፡

መቸስ ሰው የወለደውን ሲስሙለት፣ የደገሰውን ሲበሉለት፣ የጻፈውን ሲያነቡለት ደስ ይለዋልና ስንክሳር አንብቡኝ ትላችኃለች፡፡

ለማንኛውም አስተያየት ካላችሁ itaye4755@gmail.com ላይ እንገኛለን

Add post to Blinklist Add post to Blogmarks Add post to del.icio.us Digg this! Add post to My Web 2.0 Add post to Newsvine Add post to Reddit Add post to Simpy Who's linking to this post?

የአዘጋጁ መልዕክት 29 Jan 4:48 AM (last month)

 እንዴት ሰነበታችሁ? ይህ የስንክሳር ሁለተኛ እትም ነው፡፡ በመጀመርያው እትም መልካም ትውውቅ እንዳደረግን ተስፋ አደርጋለሁ፡፡ በዚያም ድረ ገጹ ላይ ባለው አድራሻ አስተያየታችሁን ብትሰጡን የበዛ ጠቀሜታ ስለሚኖረው አትርሱን፡፡ ተስማምቷችሁ ከሆነ ላይክ እና ሼር ብታደርጉ ጥሩ ነው፡፡ ሰብስክሪፕሽን የሚጀመረው በአፕሪል ስለሆነ እስከዚያው ስንክሳርን በነጻ ኮምኩሟት፡፡

    ከሁሉም በላይ ለኛ መጣጥፎች መታረም የሚገባውን ሁሉ ንገሩን፣ ራሳችሁም ከአምዶቻችን በአንዱ የራሳችሁን መጣጥፍ ብትልኩልን እንደ አስፈላጊነቱ እናወጣዋለን፡፡

በዚህ እትም በስድስት አምዶች ሰባት መጣጥፎች ይኖሩናል፡፡ 

በመጀመርያው የኢንተርናሽናል አምድ የፕሬዚዳንት ትራምፕን አዳዲስ እርምጃዎች በተመለከተ አንድ ጽሁፍ እናቀርባልን፡፡

በባህል እና ስነጥበብ አምድ ስለ አዋሽ ሰባት ኪሎ ከተማ የጀመርነው ትርክት ሁለተኛ ክፍል ይኖረናል፡፡ 

በአሰሳ አምዳችን የቮያጀር የህዋ መርከቦችን ታሪክ እናቀርባለን፡፡ ቮያጀር አንድ እና ቮያጀር ሁለት ከአርባ ሰባት አመት በፊት ወደ ጠፈር ተልከው እንስከ አሁን በስራ ላይ ያሉ የጠፈር መንኮራኩሮች ናቸው፡፡ ከምድር 25 ቢሊዮን ኪ/ሜ በላይ ርቀት ላይ ይገኛሉ፡፡ ስርአተ ጸኃይን አልፈው በይነ-ከዋክብት ወሰን ከገቡ ሰነበቱ፡፡ ይህን የሚገርም ክንዋኔ መቼም ቢቀርብ ጠቀሜታው አይቀንስም በሚል እምነት አቅርበነዋል፡፡ 

በአካባቢ ጥበቃ አምድ ከተፈጥሮ አደጋዎች እና ሙቀት አንጻር 2024 ምን አይነት አመት እንደነበረ እናብራራለን፡፡

በታሪክ አምድ ከስንክሳር አንባቢዎች ልናስተዋውቅ የፈለግነው በአለም አንደኛ ከበርቴ እና የአሁኑን ፖለቲከና ኤሎን መስክን ነው፡፡ 

በሁለተኛው አለም አቀፍ ግንኙነት አምዳችን በዚህ ወር አጋማሽ ላይ በረድ ስላለው የጋዛ ሰርጥ ጉዳይ የምንላችሁ ይኖረናል፡፡ 

በሳይንስ አምዳችን ደሞ የ 2024 የኖቤል ሽልማት አሸናፊዎችን  እናስተዋውቃችሁ እና በመጨረሻ 

በመጽሀፍ አምዳችን ፕሬዚዳንት ባራክ ኦባማ በ 2024 ከተደረሱት መጻህፍት ምርጦቹን ብለው የመደቧቸውን እንዘረዝርላችኃለን፡፡

    መልካም ንባብ!

Add post to Blinklist Add post to Blogmarks Add post to del.icio.us Digg this! Add post to My Web 2.0 Add post to Newsvine Add post to Reddit Add post to Simpy Who's linking to this post?

የ 2024 ኖቤል ሽልማት 29 Jan 4:34 AM (last month)

  በዚህ ወር የሳይንስ አምዳችን በ 2024 በሳይንስ መስኮችየኖቤል ሽልማት አሸናፊዎችን እናስተዋውቃችኃለን፡፡ በፊዚክስ፣ ኬምስትሪ እና ሜደሰን ያሸነፉት ሰዎች ዝርዝር በሁሉም የአለም መገናኛ ብዙሀን ተላልፏል፡፡ ለስክሳር አንባቢያን ፍጆታ ከ NobelPrize.org ያገኘውን የተጠናከረ መረጃ ተጠቅናል፡፡

በፊዚክስ

የዚህ አመት ተሸላሚዎች የፊዚክስን የእውቀት መሳርያዎች በመጠቀም የገነቡት ሜቶድ ለዛሬው ማሺን ለርኒንግ መሰረት ሜቶድ በመገንባታቸው ተሸላሚ ሆነዋል፡፡ ጆን ሆፕፊልድ መረጃ የሚያከማችና ሪኮንስትራክት የሚያደርግ መዋቅር በመፍጠራቸው የሽልማቱን ግማሽ ገንዘብ አግኝተዋል፡፡

ጂኦፍሪ ሂኒቶን አሁን በስራ ላይ ላለው ለላርጅ አርተፊሻል ኒውራል ኔትወርክ በጣም ጠቃሚ የሆነ በራሱ ባህርየትን በዳታ ውስጥ የሚያገኝ ሜቶድ በመፍጠራቸው የሽልማቱን ግማሽ ገንዘብ አግኝተዋል፡፡

https://www.nobelprize.org/images/165779-portrait-mini-2x.jpg

ጆን ሆፕፊልድ

ጂኦፍሪ ሂኒቶን አሁን በስራ ላይ ላለው ለላርጅ አርተፊሻል ኒውራል ኔትወርክ በጣም ጠቃሚ የሆነ በራሱ ባህርየትን በዳታ ውስጥ የሚያገኝ ሜቶድ በመፍጠራቸው የሽልማቱን ግማሽ ገንዘብ አግኝተዋል፡፡

https://www.nobelprize.org/images/165768-portrait-mini-2x.jpg

ጂኦፍሪ ሂኒቶን

በኬሚስትሪ

የ 2024 ኬሚስትሪ ኖቤል ሽልማት ያተኮረው ላይፍ ኢንጂነየስ ኬሚካል ቱልስ በፕሮቲኖች ላይ ነው፡፡ በዚህም መሰረት ዴቪድ ቤከር የማይቻለውን አዲስ አይነት ፕሮቲን ዴቨሎፕ ለማረግ በመቻላቸው የሽልማቱን ግማሽ ገንዘብ አግኝተዋል፡፡

https://www.nobelprize.org/images/165767-portrait-mini-2x.jpg

ዴቪድ ቤከር

ድሚስ ሀሳቢስ እና ጆን ጃምፐር ደግሞ

የአርተፊሻል ኢንተለጀንስ ሞዴል ዴቨሎፕ አድርገው በሱ በመጠቀም የፕሮቲንን ስትራክቸር ለመተንበይ የሚያስችል ግኝት ላይ በመድረሳቸው እያንዳንዳቸው የሽልማቱን አንድ አራተኛ ገንዘብ አግኝተዋል፡፡

https://www.nobelprize.org/images/165765-portrait-mini-2x.jpg

ዴሚስ ሀሳቢስ

https://www.nobelprize.org/images/165766-portrait-mini-2x.jpg

ጆን ጃምፐር

በሜዲሰን

የ 2024 የፊሲሎጂ ወይም ሜዲሰን ሽልማት ማይክሮአርኤንኤ ን በማግኘታው እና ማይክሮአርኤንኤ በ ፖስት ትራነሰክሪፕሽናል ጄን ሬጉሌሽን የሚጫወተውን ሚና በማሳወቃቸው ለቪክቶር አምብሮስ እ ጌሪ ሩቭኩን በጋራ ተሰጥቷል፡፡

https://www.nobelprize.org/images/165775-portrait-mini-2x.jpg

ቪክቶር አምብሮስ

https://www.nobelprize.org/images/166082-portrait-mini-2x.jpg

ጌሪ ሩቭኩን

ምንጭ

NobelPrize.org All Nobel Prizes 2024

የፕሬዚደንት ባራክ ኦባማ የ2024 ምርጥ መጽሀፍት

(ከመጽሀፍት ሰፈር)

James by Percival Everett

There’s Always This Year: On Basketball and Ascension by Hanif Abdurraqib

Everyone Who Is Gone Here  by  Jonathan Blitzer

Reading Genesis   by Marilynne Robinson

Headshot by Rita Bullwinkel

The God of the Woods  by Liz Moore 

Beautiful Days by  Zach Williams 

Martyr!  By Kaveh Akbar

💀💛 COVER REVEAL 💛💀, MARTYR! the debut novel by award-winning poet Kaveh  Akbar, is an entrancingly lyrical, blissfully macabre, utterly funny spiral  through art and love, addiction and faith, and a ...

Memory Piece  by Lisa Ko 

The Ministry of Time  by Kaliane Bradley

When the Clock Broke: Con Men, Conspiracists, and How America Cracked Up in the Early 1990s  by John Ganz

Of Boys and Men: Why the Modern Male Is Struggling, Why It Matters, and What to Do about It by Richard Reeves

The Wide Wide Sea: Imperial Ambition, First Contact and the Fateful Final Voyage of Captain James Cook

Hampton Sides

Help Wanted by  Adelle Waldman

Add post to Blinklist Add post to Blogmarks Add post to del.icio.us Digg this! Add post to My Web 2.0 Add post to Newsvine Add post to Reddit Add post to Simpy Who's linking to this post?

አኑስ ሆሪቢሊስ 29 Jan 4:24 AM (last month)

     ያለፈው የአውሮፓውያን አመት ብዙ የተፈጥሮ አደጋዎች የተስተናገዱበት አመት ነው፡፡ እዚህ አጠገባችን ስፔይን በጎርፍ አደጋ የደረሰውን ጥፋት አይተናል፡፡ ኢትዮጵያም ምድሪቱ እየንቀጠቀጠች ታስፈራራናለች፡፡ አመቱ ሲገባደድ ደግመን ደጋግመን የሰማነው የአየር ንብረት ዜና ምድራችን እንደ አምና ጨርሶ ሞቃ እንደማታውቅ ነው፡፡

     በዚች አጭር መጣጥፍ በ 2024 በአለማችን የተከሰቱትን ዋና የተፈጥሮ አደጋዎችን እና ለአደጋዎቹ መክፋት የከባቢ አየር ለውጥ ያለውን ድርሻ ለመቃኘት እንሞክራለን፡፡

     የኬራላ ግዛት ሀገር ጎብኝዎች ከሚያዘወትሯቸው ቦታዎች አንዷ ስትሆን በሕንድ ደቡብ ጠረፍ ትገኛለች፡፡ ኦገስት 20/2024ጠዋት በዌያናድ ወረዳ ኮረብታዎች  ሲጥል በቆየው ከባድ ዝናብ ላይ ከባድ የመሬት መናድ ፈጥሯል፡፡ በዚህም ሳቢያ የቀዬው ነዋሪዎች በመኝታቸው እንዳሉ ውኃ፣ ጭቃና፣ቋጥኝ ተደርምሶባቸው ሞተዋል፡፡ በአደጋው 205 ሰዎች ሲሞቱ 200ው ደሞ ጠፍተዋል፡፡ (REUTERS)

Members of the White Guard Volunteers caerry out a rescue operation in Chooralmala in Wayanad district of Kerala.

በጎ ፈቃደኞች በነፍስ አንድን ሙከራ ላይ ቾራለማላ (ዌያናድ)  World Weather Attribution

     እሌኒ አውሎ ነፋስ በደረጃ 4 የተመዘገበ ሲሆን ባለፈው ሰፕተምበር 2024 አሜሪካን፣ ኩባንና፣ ሜክሲኮን አጥቅቶ 230 ህይወት ሲቀጥፍ 55 ሚሊዮን ዶላር ንብረት አውድሟል፡፡ (Deccan Herald፣26 Dec 2024)

    አሁንም በሰብተምበር 2024 ያጊ የተባለው የእስያ ከባድ ዝናብ የቀላቀለ ነፋስ ሰሜን ቪኤትናምን መትቶ ብዙዎችን ገgድሏል. በሰአት 245 ኪ/ሜ የሚበረው ይኸው ንፋስ በደቡብ ምስራቅ እስያ ከ 800 በላይ ህይወት ቀጥፏል፡፡ (ዝኒ ከማሁ)

A group of young boys looking at a pile of trash

Description automatically generated

ታይፎን ያጊ ፎቶ UNICEF East Asia Pacific

     የጃፓን መንግስት በሬክተር ስኬል 7.6 የተመዘገበ የምድር መንቀጥቀጥ ማዕከላዊ ጃፓን ውስጥ መድረሱን ገጸ፡፡ የምድር መንቀጥቀጡ ያስከተለው ጉዳት እስከ 2.6 ትሪሊዮን የን ወይንም 17.6 ቢሊዮን ዶላር ሊደርስ እንደሚችል አስታውቋል፡፡ (KYODO NEWS )

      በቅርቡ በካሊፎርኒያ ግዛት ሎስ አንጀለስ ከተማ እና አካባቢ የደረሰውን የከፋ የእሳት ቃጠሎ አስመልክቶ ዶናልድ ትራምፕ የግዛቱን እና ከተማውን አስተዳደሮች (ሁሉም ዲሞክራቶች ናቸው) ወቅሷል፡፡ ለደረሰው የህይወት መጥፋት እና የከፋ የንብረትም እነዚሁኑ አካላት ተጠያቂ አድርጓል፡፡

      በእርግጥ እሳት አደጋው ከተነሳ በኃላ መደረግ በሚገባው ጥንቃቄ እና በጊዜ መወሰድ ከሚገባው እርምጃ አንጻር የካሊፎርኒያ ግዛትና የሎስ  አንጀለስ ከተማ መስተዳድሮች ሊጠየቁ ይገባል፡፡ ይህም ቢሆን ተገቢው ማጣራት ከተደረገ በኃላ፡፡

     ይህ ጉዳይ እንዳለ ሆኖ ዋናው የእሳት አደጋው ውድመት ከቀድሞው የከፋ መሆን ትልቁን ሚና የሚጫወተው የአለም እየሞቀች መሄድን ተከትሎ የተከሰተው የአየር ንብረት ለውጥ ነው፡፡ የአለምን እየሞቀች መሄድ (ግሎባል ዋርሚንግ) አምጪዎቹ ደሞ በፋብሪካዎች እና መኪና ጭስ ሳቢያ ወደ ከባቢ አየራችን የሚለቀቀው የካርቦንዳይኦክሳይድ መጠን መጨመር ነው፡፡ እሱም በተራው የግሪንሀውስ ጋዝ ውጤት ያመጣል፡፡

     በዚህ ረገድ ባለሙያ የሆኑ በሳሎች ወደፊት በስንክሳር ላይ ሰፋ ያለና እኛ አሁን ከምናቀርበው የተሻለ መጣጥፍ ይልኩልናል ብለን ተስፋ እናደርጋለን፡፡ እስከዚያው የግሪን ጋዝ ምን እንደሆነና ተያያዥ ውጤቶቹን በተመለከተ ‘’ናሽናል ግሪድ ግሩፕ’’ በ 23 ፌብርዋሪ 2023 ያቀረበውን ጽሁፍ ዋቢ አድርገን የሚከተለውን ለአንባቢዎቻችን ጀባ እንላለን፡፡

     እንግዲህ ግሪንሀውስ ጋዝስ (ከዚህ በኃላ GHGs ብለን የምንጠራቸው) ያው ጋዞች ሲሆኑ በከባቢ አየራችን ሙቀትን አጥምደው እንዳይተን የሚያደርጉ ናቸው፡፡

     ነገሩ እንዴት ነው? ቀን ቀን ጸኃይ በከባቢ አየራችን ላይ በማብራት የምድር ገጽን ታሞቃለች፡፡ ሌሊት ጸኃይ ስለሌለች የምድር ገጽ ይቀዘቀዝና ቀን የተቀበለውን ሙቀት ወደ አየር ይለቀዋል፡፡ ይሁንና የተወሰ አየር በከባቢ አየራችን በ GHGs ተጠምዶ እንዲቆይ ይሆናል፡፡ ይህ ነው እንግዲህ የምድራችን የአየር ጸባይ በአማካይ 14 ዲግሪ ሴንት ግሬድ ላይ እንዲረጋ የሚያደርገው፡፡

       የሰው ልጅ በዚህ አይነት እህል እየበላ ውኃ እየጠጣ፣ አንዳንዴም ጮማ እየቆረጠ ጠጅ እየጠጣ፣ ተፈጥሮም ሚዛኑን ጠብቆ ፍጥረት ለሚሊዮን አመታት በሰላም ይኖር ነበር፡፡    የግሪንሀውስ ጋዝስ በራሱ ምንም ሳንካ አልነበረውም መጠኑን እንደጠበቀ ቢቆይ ኖሮ፡፡ እህት ፕላኔታችን ማርስ ጠፍ መሬት ሆና ሙት ፕላኔት የሆነችው እኮ አንዱም በ GHGs በሚፈለገው ልክ ባለመኖሩ ነው፡፡

    ወደ ቀደመ ነገራችን እንመለስና ቀጥለን  ስለ GHGs እና ስለ ግሪንሀውስ ውጤቶች (greenhouse effect) እንመልከት፡፡ እነዚህ ግሪንሀውስ ውጤትን የሚያመጡ ጋዞች እንደ መስተዋት ግድግዳ ሆነው የከባቢአየርን ሙቀት ልኩን ጠብቆ እንዲቆይ ያደርጉታል፡፡ ልክ በዘመናዊ የአበባ እርሻዎች እንደምታዩዋቸው አረንጓዴ ሸራዎች አበባው በበዛ ጸኃይ እንዳይደርቅ፣ ሙቀት አንሶትም እንዳይጠወልግ እንደሚያደርጉት አይነት መንከባከብ እና ጥበቃ፡፡ ለዘመናዊ እርሻዎች የተጠቀምንበትን አረንጓዴ ሸራ ለከባቢ አየር ስናደርገው ግሪንሀውስ ጋዝስ ተባለ፡፡

     አለ እነዚህ ግሪንሀውስ ጋዝስ የአለማችን የአየር ጸባይ ከዜሮ በታች 18 ዲግሪ ይሆን ነበር፡፡ በዚህ -18 ዲግሪ ሴንት ግሬድ ደሞ ሕይወትን ማቆየት ባልተቻለ፡፡

    ስለዚህ እነዚህ ምድር በጣምም ሳትሞቅ በጣምም ሳትበርድ ለፍጡር የተስማማች እንድትሆን ያደረጋትን የግሪንሀውስ ጋዞች እንዳሉ ስራቸውን እንዲቀጥሉ መተው ጥሩ ነገር ነበር፡፡ ግን አልሆነም

     ቢል ኮዝቢ የተባለው ጥቁር አሜሪካዊ ኮሚክ የፊልም ተዋናይ ‘’ IS THREE A CROUD” በተባለ መጽሀፉ አንድ ተረክ አለው፡፡ 

‘’እግዚአብሄር መጀመርያ ቀን ሰማይንና ምድርን ፈጠረ፣ በሁለተኛው ቀን ጸኃይን፣ ጨረቃንና ከዋክብትን ፈጠረ፣ በሶስተኛው ቀን ዝሆንን ፈጠረ፡፡ እዚህ ላይ ቢያቆም ጥሩ ነበር፡፡ ግን አልሆነም፣ በአራተኛው ቀን ሰውን ፈጠረ!’’

      እንግዲህ ተስተካክሎ ይካሄድ የነበረ ጤነኛ አኗኗርን የሰው ልጅ ማበላሸት ያዘ፡፡ የሰው ልጅ ድርጊቶች ተፈጥሯዊ የግሪንሀውስ ኢፌክትን (ውጤትን) ቀያየረው፡፡ በዚህ ድርጊቱ የግሪንሀውስ ጋዝስ የሚለቁትን የሙቀት መጠን በአስፈሪ መጠን እየጨመሩት መጡ፡፡ ሳይንቲስቶች አሁን ግሪንሀውስ ጋዞች ለአለም ሙቀት መጨመር እና ለአየር ንብረት ለውጥ ምክንያት እንደሆኑ ይስማማሉ፡፡

      ነገሩ እንዴት መሰላችሁ? ከ 1850 የእንግሊዝ ኢንዱስትሪያል አብዮት ጀምሮ አውሮፓውያንና የተቀሩት በኃላ የመጡት ኢንዱስትሪያላዊ ሀገራት በጣም የበዛ የግሪንሀውስ ጋዞችን ወደ ከባቢ አየር መልቀቅ ጀመሩ፡፡ አስቡት እንግዲህ አንድመቶ ሰባ አምስት አመት ሙሉ በየጊዜው እየጨመረ በሚሄድ መጠን የግሪንሀውስ ጋዞቹን መጠን ከጤነኛ ልኩ እየጨመሩት ሲሄዱ፡፡

    በተለይ ባለፉት ሰላሳ አመታት ይህ ሁኔታ ተባብሶ ቀጥሏል፡፡ ነገሩን ትንሽ ለማፍታታት ያህል፣ ለመሆኑ ዋና ዋኖዎቹ የግሪንሀውስ ጋዞች የትኞቹ ናቸው?

 በመጀመርያ ዋናውን፣ ካርቦንዳይኦክሳይድ

    ካርቦንዳይኦክሳይድ በተፈጥሮአዊ ሂደቶችም ወደ አየር ይለቀቃል፡፡ ለምሳሌ እኛም እንስሳትም የምንተነፍሰው ካርቦንዳይኦክሳይድ ነው፡፡ በተጨማሪም በእሳተ ገሞራም እንዲሁ፡፡ ይሁን እንጂ በከባቢ አየር የሚገኘው የካርቦንዳይኦክሳይድ መጠን በ 50% መጠን የጨመረው ከኢንዱስትሪያዊ አብዮት መጀመር በኃላ ነው፡፡ከዚህ በተጨማሪም ሰው  እንደ ድንጋይ ከሰል፣ ንፍጣ፣ እና ነዳጅ ዘይት መሳሰሉትን የቅሬተ አካላትን ዘይቶችን ለተለያየ ጉዳይ ሲያነድ እንዲሁ ካርቦንዳይ ኦክሳይድን በገፍ ወደ ከባቢ አየር ይለቃል፡፡ የደን ቃጠሎም እንዲሁ ትልቅ የካርቦንዳይ ኦክሳይድ ምንጭ ነው፡፡

    ሌላው ምንጭ ሜቴን የተባለው አየር ነው፡፡ ሜቴን በተፈጥሮአዊ ሂደትም ይፈጠራል፡፡ ግን ሰውም ቢሆን ለጥፋት ስራ አይፈታምና፣ በከብት እርባታ ሂደት፣ በቁሻሻ አደፋፍ፣ በሩዝ እርሻ ሂደትም ሰው ሜቴንን ወደ ከባቢ አየር በበዛ መጠን ይለቃል፡፡

    ሶስተኛው ምንጭ ኒትሮስ ኦክሳይድ ይባላል፡፡ ይህ ጋዝ በከፍተኛ መጠን ወደ አየር የሚለቀቀው በኬሚካል እና ኦርጋኒክ ማዳበሪያነት ሂደት፣ ራሱ ጋዙንም በማምረት እና በባዮማስ ማቀጣጠል ሂደት ነው፡፡

     ጤዛም እንዲሁ ባይበዛም ለግሪንሀውስ ጋዝስ የራሱ አበርክቶ አለው፡፡

     የግሪንሀውስ ጋዝስን ለመቀነስ ምን እናድርግ?

     ሁሉን ጥረት በማድረግ በ 2050 የካርቦንዳይኦክሳይድ አጠቃቀማችንን በ 2050 ዜሮ ለማድረግ እንቻል፡፡ ማህበረሰቡ በተቻለ መጠን የካርቦንዳይኦክሳይድ ተጠቃሚነቱን እንዲቀንስ ማድረግ ለከባቢ አየር ደህንነት ትልቅ አስተዋጽዖ ነው፡፡

     መድረስ ያለብን ግን ትንሽ ካርቦን፣ ብዙ ታዳሽ የኃይል ምንጭ ተጠቃሚ የሆነ አለም መፍጠር ነው፡፡ ለዚህም የቴክኖሎጂ አቅማችንን አዳብረን ከካርቦን ነጻ በሆነ የኤሌክትሪክ ኃይል ለመስራት መቻል፡፡ (national grid group,)

    የኤሌክትሪክ መኪናዎች አምራች ኩባንያ ባለቤት ኤሎን መስክ የዶናልድ ትራምፕ ዋና ባለሟል መሆን ትራምፕ ስለ አየር ንብረት ለውጥ ያለውን ግንዛቤ ለማስቀየር ከረዳ በጣም ጥሩ ነበር፡፡ ዶናልድ ትራምፕ አቋሙን ለመቀየር የማይችል ሰው አይደለም፡፡ በቲክ ቶክ ላይ ያደረገው ቀኝ ኃላ ዙር ለውጥ ጥሩ ማሳየያ ነው፡፡

    ስንክሳር ለአንባቢዎቿ ይህን በተመለከተ የራሳቸውን አስተዋጽዖ አሳንሰው እንዳይመለከቱ ለማሳሰብ ትወዳለች፡፡ እያንዳንዳችን አቅም ካለን የኤሌክትሪክ መኪና ብንጠቀም፣ በቁሻሻ አጠቃቀም ረገድ አስፈላጊውን ጥንቃቀቄ ብናደርግ፣ በተቻለን መጠን የፕላስቲክ አጠቃቀማችንን ብንቀንስ ትንሽ ነገር አይደለም፡፡ ከሰል ለምግብ ማብሰያነትም ሆነ ለሙቀት አለመጠቀም፡፡ የአካባቢ ጥበቃን ከግምት ውስጥ አስገብተው የተሰሩ ነገሮችን መርጦ በመግዛት፣ እንዲሁም ታዳሽ ነገሮች ለምሳሌ የተጠቀምንባቸውን ፕላስቲክ ነገሮች አድሰው ለሚሰሯቸው አካላት ለማስረከብ ብንችልም እንዲሁ፡፡

     በአለም አቀፍ ደረጃ ከተሄደ ደሞ ዋናው የ2016ቱ የፓሪስ ስምምነት ነው፡፡ ብዙዎቻችሁ ስለዚህ ስምምነት ሰምታችሁም አንብባችሁም ታውቁ ይሆናል፡፡ ዘ ይኾነ ኾይኑ – ያወቃችሁም እንድታስታውሱት፣ በደንብ የማታውቁትም የተሻለ ግንዛቤ እንዲኖራችሁ፣ የማታውቁትም እንድታውቁት ስለ ፓሪስ ስምምነቱ የሚከተለውን ለጤናችን!

      የፓሪስ ስምምነት የህግ አሳሪነት ያለው በአየር ንብረት ለውጥ ላይ የተደረገ አለም አቀፋዊ ስምምነት ነው፡፡ ፓሪስ ላይ በ2016  የተባበሩት መንግስታት የአየር ንብረት ለውጥ ኮንፌራንስ (COPC21) ባደረገው ስብሰባ የተደረሰበት ስምምነት ሲሆን 196 አገራት በፊርማቸው አጽድቀውታል፡፡

A group of people in suits

Description automatically generated

የፓሪስ ስምምነት ተፈራራሚዎች

      የስምምነቱ ዋና ግብ የአለምን የሙቀት መጠን ከ ቅድመ-ኢንደስትሪያል መጠን  ከ2 ዲግሪ ሴንቲግሬድ በታች እንዲይሆን ማድረግ፣ እንዲሁም የአየር ንብረት መወሰኛ ነጥብን ቅድመ-ኢንደስትሪያላይዜሽን ከ 1.5 በላይ እንዳይጨምር መገደብ፡፡

     ይሁን እንጂ ከቅርብ አመታት ወዲህ፣ የአለም መሪዎች በዚህ ምዕተ አመት መጨረሻ፣ የአለምን ሙቀት (ገሎባል ዎርሚንግ) መጠን ከቅድመ – ኢንዱስትሪያላዊ መጠን 1.50 C ብቻ በልጦ እንዲገኝ ማድረግ አስፈላጊ መሆኑን አስምረውበታል፡፡

      ይህም የሆነበት ምክንያተት የተባባሩት መንግስታት በይነ-መንግስታዊ ፓኔል የ1.50 C ገደብ ማለፍ እንደ አደገኛ ድርቅ፣ የሙቀት ሞደጎች እና እጅግ ከፍተኛ ዝናብ የመሳሰሉ መቅሰፍቶችን ሊያስከትል እንደሚችል  በመጠቆማቸው ነው፡፡ (UNITED NATION CLIMEATE CHANGE)

A group of people raising their hands

Description automatically generated

High Res pictures

ምንጮች

Deccan Herald፣26 Dec 2024

KYODO NEWS – Jan 25, 2024 

national grid group, February 23 2023

REUTERS By Munsif Vengattil, Chris Thomas and Jose Devasia፣ August 2, 20242

World Weather Attribution፣ 14 August, 2024

UNITED NATION CLIMEATE CHANGE – Process and meetings – The Paris Agreement.

Add post to Blinklist Add post to Blogmarks Add post to del.icio.us Digg this! Add post to My Web 2.0 Add post to Newsvine Add post to Reddit Add post to Simpy Who's linking to this post?